በተያዘው የትምህርት ዓመት ከ170 ሺህ በላይ ተማሪዎች ይመረቃሉ- ትምህርት ሚኒስቴር

84
አዲስ አበባ ሰኔ 21/ 2010 በ2010 የትምህርት ዘመን ከ170 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚመረቁ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። ተመራቂ ተማሪዎቹ ወደ ማህበረሰቡ በሚቀላቀሉበት ጊዜ በፍቅርና በመደመር እሳቤ ለአገራቸው ሰላምና ብልጽግና እንዲተጉ ጥሪ አቅርቧል። የሚኒስቴሩ የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ ሐረጓ ማሞ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በትምህርት ዘመኑ በመደበኛውና ከመደበኛ ውጭ በሆኑ የትምህርት መርሃ ግብሮች 170 ሺህ 578 ተማሪዎች እንደሚመረቁ ይጠበቃል። ከአርባ በላይ ከሆኑ የመንግስት ከፍተኛ ተምህርት ተቋማት የሚመረቁት ተማሪዎቹ፤ 116 ሺህ 129 በመደበኛ መርሃ ግበር ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን 54 ሺህ 450 ያህሉ ደግሞ መደበኛ ባልሆኑ መርሃ ግብሮች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ናቸው። ከተመራቂዎቹ መካከል 790ዎቹ በሶስተኛ ዲግሪ፣ 21 ሺህ 581 በሁለተኛ ድግሪ፣ 148 ሺህ 207 ደግሞ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ናቸው። ከተመራቂዎቹ መካከል 32 በመቶዎቹ ሴቶች ናቸው። ተመራቂ ተማሪዎቹ ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ በተማሩባቸው የትምህርት መስኮች በተፈጠረው የስራ ዕድል ገብተው እንዲሳተፉ ጥሪ አድርገዋል። ''በትምህርት ዘርፉ ያሉ አጠቃላይ ሰራተኞች፣ መምህራንና ተማሪዎች በመደመር እሳቤ ውስጥ አብረው የሚራመዱ ናቸው'' ያሉት ወይዘሮ ሐረጓ፤ መንግስት እየወሰዳቸው ያሉ የዕርቅ፣ የሰላም፣ የፍቅርና ሌሎች መልካም እሳቤዎችን በመከተል አገሪቱን ማልማት ይጠበቃል ብለዋል። በተለይም አገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ በውል በመረዳት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን የመደመርና የፍቅር መንገድ መከተልና አገርን መምራት የሚያስችል ሰብዕና መላበስ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ከትምህርት ተቋማት ወጥቶ ህብረተሰቡንና አገሩን የሚያለማ ወጣት ከትምህርትና ስልጠና ዕውቀቶቹ ባሻገር ለአገር ፍቅር እንዲኖረውና የተሟላ ስብዕና ያለው የተማረ ኃይል ለማፍራት ከስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት ማሻሻል ጀምሮ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል። ሚኒስቴሩ በትምህርት ሽፋን ከፍተኛ ስኬታማ ስራዎችን እያከነወነ መሆኑን ገልጸው፤ በትምህርት ጥራት በኩል የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት እየተደረገ ያለው ጥረት በትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም