የሲመተ-ክህነት በዓል ቤተክርስቲያኗ ከሌሎች አገራት ተጽዕኖ የወጣችበት ነው

87

አዲስ አበባ፣ ካቲት 24/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዓመታዊ የሲመተ-ክህነት በዓል ከዘመናት ተጋድሎ በኋላ ከሌሎች አገራት ጳጳሳት ተጽዕኖ ወጥታ ነጻነቷን ያወጀችበት መሆኑን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ተናገሩ።

የብጹዕ አቡነ ማቲያስ ሰባተኛ ዓመት በዓለ ሲመት ዛሬ ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እስከ 1951 ዓ.ም ድረስ የራሷን ባህልና ቋንቋ በማያውቁ የውጭ አገር ዜግነት ባላቸው ጳጳሳት ስትመራ ቆይታለች።

አቡነ ማቲያስ በበዓለ ሲመታቸው ላይ “የየትኛውም ሹመት ዓላማ የተሾመለትን ወገን በእኩልነትና በእውነት ማገልገል ቢሆንም እስከ 1951 ዓ.ም ቤተክርስቲያኗ የራሷን የሐይማኖት አባቶች መሾም ባለመቻሏ ታሪካዊ ድክመት አስከትሏል” ብለዋል።

ይህም የቤተ ክርስቲያኗን አገልግሎትና ሠላማዊ ተሳትፎ ገድቦ እንደነበር አስታውሰው አሁን ቤተ-ክርስቲያኗና መንግስት በመመካከር የተሻሉ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

መንግስት የቤተ-ክርስቲያኗን የይዞታ ባለቤትነት በማረጋገጥ፣ የተወረሱ ህንጻዎቿን በመመለስና በሌሎች አህጉራትም ተቀባይነት እንድታገኝ በማድረግ ረገድ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አውስተዋል።

ያም ሆኖ አሁንም ቀሪ ስራዎች እንዳሉ ጠቁመዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች በምዕመናንና በቤተክርስቲያን ንብረቶች ላይ ችግሮች ቢፈጠሩም ቤተክርስቲያኗ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑንም ገልጸዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ የከተማዋን ምክትል ከንቲባ ወክለው ባደረጉት ንግግር "በዓለ ሲመቱ ዳግም እንደ አድዋ ሊከበር የሚገባው የነጻነት ቀን ነው" ብለዋል።

ይህም የአገሪቷን ባህልና ቋንቋ የሚያውቁ፤ ህዝቡን የመሰሉ አባቶች ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኙበት በዓል መሆኑንም ነው ያስረዱት።

የከተማ አስተዳደሩ የቤተ-ክርስቲያኗን ይዞታ ለማስጠበቅና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በቅርበት እየሰራ መሆኑንና ይህም እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ የቤተክርስቲያኗ 6ኛው ጳጳስ ሲሆኑ የመጀመሪያውና በ1951 ዓ.ም የተሾሙት ደግሞ አቡነ ባስልዮስ ናቸው።

ይህ በዓለ ሲመት ከ1951 ዓ.ም ጀምሮ በሲኖዶሱ ውሳኔ የቤተክርስቲያኗ ዋና በዓል ሆኖ እንዲከበር ውሳኔ መተላለፉ ተገልጿል።

በበዓለ ሲመቱ የቤተክርስቲያኗ፣ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራሃላፊዎች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም