በመስኖ ልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን በሀድያ ዞን የባድዋቾ ወረዳ አርሶአደሮች ገለጹ

81
  ሀዋሳ ሚያዚያ 26/2010 በአካባቢያቸው የተገነባው የመስኖ ግድብ የጓሮ አትክልትና በቆሎ በማምረት ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን የሀድያ ዞን ምዕራብ ባድዋቾ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡ አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጡ አርሶ አደሮች እንዳሉት በአካባቢያቸው የተገነባውን መስኖ በመጠቀም የተለያዩ ሰብሎችና የጓሮ አትክልቶችን በማልማት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በወረዳው ሀዎራ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር ታሪኩ ጌዴቦ ከሁለት ዓመት በፊት የተገነባው የሀዎራ አነስተኛ የመስኖ ግድብ እርሳቸውን ጨምሮ በርካታ የቀበሌውን አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ በማድረግ ኑሯቸውን እየለወጠ ነው፡፡ በቆሎ፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲምና ሌሎች የጓሮ አትክልቶችን በዓመት ሦስት ጊዜ በመስኖ ማልማታቸው የተሻለ  ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑንም ተናግረዋል። አርሶ አደሩ እንዳሉት ቀደም ሲል በባህላዊ መንገድ ከወንዝ ውሃ ቀድተው  በአነስተኛ መደብ ላይ ሲያለሙ ቢቆዩም በጣም አድካሚ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ዘንድሮ ሁለት ጊዜ ምርት ሰብስበው በመሸጥ 28 ሺህ ብር ማግኘታቸውን የገለጹት አርሶ አደር ታሪኩ፣ ለሦስተኛ ጊዜ ካለሙት ቀይ ሽንኩርት 15 ኩንታል ድንችና 10 ኩንታል በቆሎ ምርት አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡ ሌላዋ አርሶ አደር ብዙነሽ ታሪኩ በበኩላቸው ባላቸው አነስተኛ ማሳ ላይ ቀይ ሽንኩርት፣ ጥቅል ጎመንና ድንች በዓመት ሦስት ጊዜ እያለሙ ኑሯቸውን መለወጥ እንደቻሉ ነው የገለጹት፡፡ በመስኖ የሚያለሙትን የጓሮ አትክልት ከቤት ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ በአንድ ዙር ብቻ ከ3 እስከ 6 ሺህ ብር እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡ የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ እዩኤል ታደሰ በበኩላቸው በምርት ዘመኑ በሦስት ዙር ከ53 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎችና የጓሮ አትክልት መልማቱን ነው የገለጹት፡፡ ከስድስት ዓመት በፊት በዞኑ በመስኖ የሚለማው መሬት መጠን ከአንድ ሺህ 400 ሄክታር ይበልጥ እንዳልነበር አስታውሰዋል። አቶ እዩኤል አንዳሉት፣ የውሃ አማራጮች በቅርበት ቢኖሩም ያሉትን የመስኖ ተቋማት ሙሉ በሙሉ መጠቀም ባለመቻሉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ሳይቻል ቆይቷል። በተሳትፏዊ አነስተኛ የመስኖ ልማት መርሃ ግብር በአራት የዞኑ ወረዳዎች ከ222 ሄክታር በላይ መሬት ማልማት የሚያስችሉ አራት የመስኖ ግንባታዎች መከናወናቸውንና ሦስቱ ተጠናቀው ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል። "ከእዚህ በተጨማሪ ለአርሶ አደሩ ስልጠና በመሰጠቱ በአሁኑ ወቅት የመስኖ ተጠቃሚዎች ቁጥር እያደገ መጥቷል" ብለዋል፡፡ በደቡብ ክልል የምግብ ዋስትና ችግር ባለባቸው 34 ወረዳዎች የተመረጡ አርሶ አደሮችን ስልጠና በመስጠትና ግብዓት በማቅረብ በምርምርና በማምረት ሥራ እንዲሳተፉ መደረጉን የገለጹት ደግሞ የክልሉ የተሳትፏዊ አነስተኛ የመስኖ ልማት መርሃ ግብር አስተባባሪ አቶ ምራ መሀመድ  ናቸው፡፡ በመጀመሪያው ዙር ከ180 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ 17 የመስኖ ተቋማት በክልሉ መገንባታቸውን የጠቆሙት አስተባባሪው፣ በተያዘው ዓመት 11 ተጨማሪ ተቋማትን ለመገንባት ከ236 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦ ቅድመዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ከእዚህ ጎን ለጎን የመስኖ ተቋማቱ በደለል ተሞልተው የአገልግሎት ጊዜያቸው እንዳያጥር ለተፋሰስ ልማት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አቶ ምራ አስረድተዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም