በባሌ ዞን ገበያ ተኮር ለሆኑ ምርቶች የገበያ ትስስር ለመፍጠር እየተሰራ ነው

76

ጎባ፣ የካቲት 24/2012 (ኢዜአ) በባሌ ዞን ገበያ ተኮር የስንዴና ሌሎች ምርቶች የገበያ ትስስር በመፍጠር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ የገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡


በፓስታና መካሮኒ ስንዴ ልማት የተሳተፉ አርሶ አደሮች ተወካዮችና ምርቱን በግብዓትነት የሚጠቀሙ የፋብሪካ ባለቤቶች የገበያ ትስስር የመግባቢያ ሰነድ በባሌ ሮቤ ተፈራርመዋል፡፡ 

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ተወካይ አቶ አህመድ መሐመድ እንደተናገሩት በዞኑ ለሚመረተው የሰብል፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት የገበያ ትስስር በመፍጠር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡

የገበያ ትስስሩ የሚፈጠረው አርሶ አደሩ የሚያመርተውን የተለያየ ዓይነት የግብርና ምርቶችን ከዩኒቨርሲቲ፣ ከማረሚያ ቤቶች፣ ከዱቄት፣ ዳቦ፣ ፓስታና መካሮኒ ፋብሪካዎች ጋር ነው፡፡ 

ሌሎች በዞኑ የሚገኙ ዩኒየኖችና የህብረት ስራ ማህበራት የአርሶ አደሩን ምርት ተረክበው እጥረት ወደ አለባቸው አካባቢዎች አጓጉዘው ለተጠቃሚዎች እንዲያቀርቡም የተጀመረው የገበያ ትስስሩ ጥረት እንደሚቀጥል አቶ አህመድ ገልጸዋል።

ከገበያ ትስስሩ ተጠቃሚዎች መካከል በሲናና ወረዳ የሰቆ ጀፈራ የአርሶ አደሮች ህብረት ስራ ማህበር ኃላፊ አቶ የቦ ሀጂ መሐመድ እንዳሉት  ከዚህ በፊት በአባል ማህበራት የሚመረተውን የፓስታ ስንዴ ተገቢውን የገበያ ትስስር ስለማያገኙ የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ አልነበሩም፡፡

በአሁኑ ወቅት  ሆራና አልቪማ የሚባሉ የምግብ ፋብሪካዎች ጋር ከአባላቶቻቸው የተረከቡትን 4 ሺህ ኩንታል የፓስታና መካሮኒ ስንዴን ለማቅረብ የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ተናግረዋል።

"ከአምራቹ ጋር በቀጥታ እንዲንገናኝ የተፈጠረልን የገበያ ትስስር አርሶ አደሩ ተገቢውን የምርት ዋጋ እንዲያገኝ ከማድረጉም ባሻገር ከዚህ በፊት በደላሎችና ህገ ወጥ ነጋዴዎች ያጋጥም የነበረውን የጥራት ችግር ያስቀራል "ያሉት ደግሞ የአልቪማ ፉድ ኮምፒሌክስ ፋብሪካ የጥራት ማኔጀር አቶ ደሳለኝ ሰቀላ ናቸው፡፡

አምራቹና ገዥው  የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን በምርምር ፣የምርት ጥራት ደረጃና የፕሮቲን ይዘት መለየት ላይ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል ተወካይ አቶ አማረ ቢፍቱ ናቸው።

"ማዕከሉ ድሬ፣ ቡላላና ኤጀርሳ የሚባሉ የፓስታና መካሮኒ የስንዴ ዝሪያዎችን በምርምር በማውጣት ለተጠቃሚው አድርሷል" ብሏል፡፡ 

የምርምር ውጤቶችን ማውጣት ብቻውን ግብ እንዳልሆነ ያመለከቱት አቶ አማረ ፤ አርሶ አደር ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ ካመረተው የልፋቱን ያህል  ዋጋ እንዲያገኝ የሚያስችል እየተሰራ ነው ብለዋል።

በገበያ ትስስር ዙሪያ ከሚሰሩ እንደ ኢትዮ-ኢጣሊያ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በባሌ ዞን በ2011/2012  የመኽር ወቅት በተለያዩ የሰብል ዘር ከለማው ከ340ሺህ ሄክታር በላይ መሬት 49 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆነው የዳቦ፣ ፓስታና መካሮኒ ስንዴ መሆኑን ከዞኑ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም