የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ በሳይንስ ሊደገፍ ይገባል

87

ሐዋሳ፣ የካቲት 24/2012 (ኢዜአ) የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ ውጤታማና ዘላቂ መፍትሄ እንዲያመጣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሣይንስ ምርምር ሊደገፉ እንደሚገባ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሓዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሐዋሳ ሐይቅን ከደለልና ከሌሎች አደጋዎች ለማዳን በሲዳማ ዞን ቦርቻ ወረዳ በ15 ሄክታር የተጎዳ መሬት ላይ እያከናወነ ያለውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ከመላ ሃገሪቱ በተውጣጡ የዩኒቨርስቲዎች አመራሮችና በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተጎብኝቷል።

በዚህ ወቅት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሴር አፈወርቅ ካሱ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲዎች ወደታች ወርደው የህብረተሰብን ችግር የሚፈቱ የሳይንስና የምርምር ስራዎችን ሊሰሩ ይገባል።

በዚህ ረገድ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ እየተከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው ፤ በተለይ በየደረጃው በህዝብ ተሳትፎ የሚሰሩ የአፈርና ውሃ እቀባ ልማቶች ውጤት እንዲያመጡ ዩኒቨርስቲዎች ሃገር በቀል ዕውቀትና ጉልበት በመጠቀም ሳይንሳዊ መፍትሄ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱም ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ ተፈጥሮአዊ ዕውቀቶችን ከዘመናዊ አስተሳሰብ ጋር አገናኝቶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል የሳይንስ ባህል ግንባታ ለማከናወን አደረጃጀት ፈጥሮ ስራ ውስጥ መግባቱን ገልጸዋል።

የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶክተር ራሕመቶ አበበ የሃዋሳ ሃይቅ በደለልና በመሰል ጉዳዮች እየደረሰበት ያለውን ጉዳት ለመከላከል እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተለይ በሀይቁ ዙሪያ በሰውና በተፈጥሮ የተጎዱ አካባቢዎችን በመለየት መልሶ እንዲያገግም ለማድረግ በሣይንስ የተደገፈ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ካለፈው ዓመት ወዲህ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ የአካባቢውን ማህበረሰብ በማስተባበር ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጥ በሚችል መልኩ ከ40 ሄክታር በላይ የተጎዳ መሬት ቦርቻና ወንዶገነት ወረዳዎች ውሰጥ በመከለል የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ሃይቁን በደለል ከመሞላት አደጋ ከመከላከል ባለፈ አካባቢው ወደ ነበረበት ተፈጥሮአዊ ይዘት በመመለስ ለእርሻና ለግጦሽ እንዲውል የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

ተዳፋታማ የሆነ አካባቢያቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ በጎርፍ ምክንያት እየተቦረቦረ በመጎዳቱ ተስፋ ቆርጠው እንደነበር የሚናገሩት ደግሞ በሲዳማ ዞን ቦርቻ ወረዳ ይርባ-ዱዋንቾ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ንጉሴ ዶንጋቶ ናቸው፡፡

እሳቸው እንደሚሉት አሁን ላይ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ ከጀመረ ወዲህ በተጨባጭ ለውጥ በማስገኘቱ ተስፋ ሰንቀዋል።

ሌላኛው የአከባቢው ነዋሪ አቶ ላምሶ ላጬ በበኩላቸው አካባቢው በመራቆቱ በርካቶች ቤታቸውን አፍርሰው እንደሸሹ ገልጸው ፤ በተሰራው ስራ አሁን ላይ ውጤት በማየታቸው ተፈጥሮን ለመንከባከብ ትምህርት መውሰዳቸውን ነው የተናገሩት፡፡

በሲዳማ ዞን የቦርቻ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት የተፈጥሮ ሃብትና አነስተኛ መስኖ ልማት ቡድን መሪ አቶ ክፍሌ ደስታ በወረዳው ይርባ ዱዋንቾ ቀበሌ ያለው 15 ሄክታር መሬት መራቆቱ አስፈሪ እንደነበር ጠቅሰው ፤ ከዩኒቨርስቲው ጋር በመተባበር በተሰራው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ አካባቢው ሊያገግም ችሏል።

በተከናወኑ ስነ አካላዊ ስራዎች የአካባቢው ልምላሜ በመመለሱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተለያዩ ዕጽዋቶች መብቀል መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም