ዕርቀ ሰላሙ በጠንካራ መሰረት የታነፀና የሁለቱንም ህዝቦች ዘላቂ ሰላም የሚያረጋግጥ ሊሆን ይገባል - የኃይማኖት አባቶች

65
አዲስ አበባ ሰኔ 21/2010 የኢትዮጵያና ኤርትራ ዕርቀ ሰላም በጠንካራ መሰረት ላይ የታነፀና የሁለቱንም ህዝቦች ሰላም የሚያረጋግጥ እንዲሆን የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች አሳሰቡ። የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች የኢትዮጵያና የኤርትራን ዕርቀ ሰላም ሂደት አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል። የሁለቱም አገራት መሪዎች ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የወሰዱት በጎና አዎንታዊ  አቋም እጅግ የሚበረታታ ሆኖ እንዳገኙት በመግለጫቸው አስታውቀዋል። በሁለቱ አገሮች መካከል ላለፉት 20 ዓመታት የቆየውን አለመግባባት በእርቅና በሰላም ለመፍታት የተጀመረውን ጥረትም በአድናቆት እንደሚቀበሉትም ገልፀዋል። የተጀመረው የሰላም ሂደት በአገራቱ መካከል አዲስ የሰላም ምዕራፍ መክፈቱን ገልጸው የሁለቱን አገራት ኃይማኖታዊ ትስስር ያጠናክረዋልም ብለዋል። ከዚህ በላይም በህዝቦቹ መካከል ለዓመታት ተፈጥሮ የቆየውን መጠራጠር፣ አለመግባባትና ስጋት ሙሉ ለሙሉ ያስወገደ ውሳኔ መሆኑን አብራርተዋል። ይሄ ጫፍ ላይ የደረሰው የዕርቅና የሰላም ሂደት ሰላም ወዳዱን የሁለቱ አገራት ህዝብ ግንኙነት የሚያለመልምና ተስፋ የሚሰጥ እንደሆነም በመግለጫቸው አረጋግጠዋል። ዕርቀ ሰላሙ ዕውን ሆኖ የሚፈለገውን ዘላቂ ሰላም እንዲያመጣ የእርቅ ሂደቱ በጠንካራ መሰረት ላይ የታነፀና የሁለቱ አገራት ህዝቦች የሚፈልጉትን ሰላም የሚያረጋግጥ እንዲሆንም ነው የበላይ ጠባቂዎቹ ያሳሰቡት። ከዕርቀ ሰላሙ ጎን ለጎን በሁለቱ አገራት መካከል ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መፍጠርና ማጠናከር አስፈላጊ ነውም ብለዋል። የእርቅ ሂደቱ እውን እንዲሆንም በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ምዕመናንን ጨምሮ የኃይማኖት አባቶችና አስተማሪዎች ስለሰላም፣ ፍቅርና ይቅርታ በማስተማር መንፈሳዊና አባታዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። ሁሉም የኃይማኖት ተቋማት  ስለሰላም፣ ፍቅርና ይቅርታ በመስበክ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ በመግለፅ ጉባኤው የሚፈለግበትን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን የጉባኤው የበላይ ጠባቂ አባቶች  አረጋግጠዋል። የሰላም ሂደቱ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያስገኝም የኤርትራ የኃይማኖት አባቶች የድርሻቸውን መንፈሳዊ ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም