ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳኢያስ አፈወርቂ መልዕክት ላኩ

101
አዲስ አበባ ሰኔ 21/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳኢያስ አፈወርቂ ዛሬ መልዕክት ላኩ። ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ በኢትዮጵያ የነበረውን ቆይታ አጠናቆ ዛሬ የሚመለሰውን የኤርትራ መንግስት ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እንደገለጹት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኤርትራ መንግስት ከፍተኛ ልዑካን በኩል ለፕሬዝዳንት ኢሳኢያስ መልዕክት ልከዋል። ሁለቱ አገሮች ወደፊት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከርና ኤምባሲ መክፈት በሚቻልበት ሁኔታ የመከሩ ሲሆን ወደፊት በፖለቲካ መስክ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚያዊ መስክ አብሮ መስራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ውይይት እንደሚያካሂዱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተናግረዋል። የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በቅርቡ በመሪዎች ደረጃ ውይይት እንደሚያደረግም ገልፀዋል። አዲስ አበባ ላይ ከኤርትራ መንግስት ከፍተኛ ልዑክ ጋር የተደረገው ውይይት በሁለቱ ሀገራት መካከል ማምጣት ለሚፈለገው ሰላም ምቹ እድል የፈጠረ መሆኑም ተገልጿል። በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የሁለትዮሽ ውይይት ሲካሄድ ከ20 ዓመታት በኋላ የአሁኑ የመጀመሪያው ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም