የአፍሪካ ህብረት የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎችን የተኩስ አቁም ስምምነት አደነቀ

59
ሰኔ 21/2010 የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች ተኩስ ለማቆና ለሀገሪቱ ሰላም ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን አድንቀዋል፡፡ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርና የተቀናቃኝ መሪው ሬክ ማቻር በ72 ሰዓታት ውስጥ ተኩስ ለማቆም ትናንት ካርቱም ላይ መስማማታቸውን ተከትሎ ኮሚሽኑ መግለጫ አውጥቷል፡፡ ሊቀመንበሩ ሙሳ ፋኪ ማሃመት የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ያገባናል የሚሉ አካላት በሁለቱ ወገኖች በተፈረመው ስምምነት መሰረት የሀገሪቱ ዜጎች ስቃይ እንዲያበቃ ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት፡፡ ለሰላምና እርቁ ዘላቂነት ኢጋድ እና የአፍሪካ ህብረት የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተግባራዊነት ክትትል እንዲያደርግ መስማማታቸውም ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል፡፡ ሙሳ ፋኪ የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦመር ሀሰን አልበሽር እና የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ላበረከቱት አስተዋጽኦም አመስግነዋቸዋል፡፡ የኮሚሽኑ ሊቀመንበር የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ተቀናቃኛቸው ሬክ ማቻር በሀገሪቱ ሰላም ለማስፈን የጀመሩትን የፊት ለፊት ውይይት የአፍሪካ ህብረት ሙሉ በሙሉ ይደገፋል ነው ያሉት፡፡ ህብረቱ በደቡብ ሱዳን እርቀ ስላም እንዲወርድና  ፀጥታ እንዲሰፍን ከኢጋድ ጋር በቅርበት ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም