በጎ አድራጊው ለተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ድጋፍ እያደረጉ ነው

131

ድሬዳዋ፣ የካቲት 22/2012 (ኢዜአ) የአቅመ ደካሞች ቤተሰብ የሆኑ 560 ህጻናት ተማሪዎችን በምገባ ፕሮግራም ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን አቶ ወሰን ቢራቱ የተባሉ በጎ አድራጊ ገለጹ።

የድሬዳዋ ተወላጅ የሆኑት በጎ አድራጊው ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ላለፉት ሶስት ዓመታት በምግብ ዕጥረት ሣቢያ ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ  ተማሪዎችን ለመታደግ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

በአሁን ወቅትም በስምንት ትምህርት ቤቶች የሚገኙ 560 ህጻናት ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ለቁርስ የሚሆን ወጪ በመሸፈን ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በወር 75 ሺህ ብር ወጪ እንደሚያደርጉ ጠቅሰው  ጓደኞቻቸውና አንዳንድ በጎ አድራጊ ተቋማት ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ጠቅሰዋል።

"የድሬዳዋ አስተዳደር 100 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጎልኛል፤ የትምህርት ቢሮ ሁልጊዜም እየደገፈኝ ነው" ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉካ መሐመድ "ግለሰቡ እያበረከቱ የሚገኘው በጎ  ተግባር በአርአያነት የሚጠቀሱና የሚመሰገኑ ነው" ብለዋል፡፡

ይህ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ባለሃብቶች የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

እንደ መንግስት የድሬዳዋ አስተዳደር በገጠር በጀልደይሣ ክላስተር የጀመረውን የምገባ ፕሮግራም በቀጣይ ችግረኛ ተማሪዎች በሚገኙባቸው ትምህርት ቤቶች በቋሚነት ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የድሬዳዋ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮች የምግብ ፕሮግራም ከሚከናወንባቸው መካከል በመሐመድ አብዱላሂ ኦክሰዴ መታሰቢያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው ተማሪዎቹን ተመልክተዋል፡፡

የጉባኤው ሰብሳቢ ሊቀ ብርሃናት ቀለመወርቅ ቢምረው "ችግረኛ ህጻናትን መርዳትና መደገፍ ምድራዊም ሆነ ሰማያዊ ፀጋን ያላብሳል" ብለዋል፡፡

ይህን ተግባር ለማጠናከር ችግረኛ ህጻናት ተደራሽ ለማድረግ ሁሉም በአቅሙ እንዲደግፍ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአምስተኛ ክፍል ተማሪ አብዲ አሜ አባቱን በሞት ካጣ ወዲህ ለሁለት ዓመታት ትምህርት ያቋረጠው በምግብ እጥረት እንደነበር አስታውሶ አሁን ግን በተፈጠረው ምቹ አጋጣሚ ወደ ትምህርት መመለሱን ተናግሯል፡፡

ከቁርስ በተጨማሪ  ምሳ የሚያገኙበት መንገድ ቢመቻች የበለጠ ደስተኛ ሆነው እንደሚማሩም አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም