የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል ላይ ትኩረት ያደርጋል - የጤና ሚኒስቴር

148

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 21/2012 (ኢዜአ) በቀጣይ የሚተገበረው የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ የጤና ሚኒስቴር አመለከተ።

የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ በገጠር ቀበሌዎች በተመረጡ 16 የጤና ፓኬጆች ሲተገበር ቆይቷል።

በዋናነትም የአገሪቱ የጤና ፖሊሲ ትኩረት በሆነው የበሽታ መከላከል ላይ የላቀ ውጤት ማስመዝገብ የቻለና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተሞክሮ የወሰዱበት መሆኑ ይታወቃል።

መርሃ ግብሩ ሲቀረጽ ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የደረጃ እድገት ጋር እና በፓኬጅ ከተያዙ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ክፍተት በማጋጠሙ ከቅርብ አመታት ወዲህ እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ ማነቃቃት እንደሚያስፈልግ ታምኖበት እየተሰራ ይገኛል።

በጤና ሚኒስቴር የጤና ኤክስቴንሽን ኦፊሰር አቶ ካሳሁን በፈቃዱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምን በማጠናከር ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳካት ጥረት እየተደረገ ነው።

በተለይም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎች ላይ ትኩረት መደረጉን አብራርተዋል።

የስኳር በሽታ፣ የደም ግፊትና ካንሰር የመሳሰሉትን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የአኗኗር ዘይቤን ለማሻሻል በጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር ተካቶ እንደሚሰራበት ጠቁመዋል።

በጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር ትግበራ ሂደት ውጤት የመጣባቸውን ጉዳዮችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የባለሙያዎችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ አሰራር እንደሚኖርም አቶ ካሳሁን ገልጸዋል።

በዚሁ መሰረት የጤና አገልግሎት ጥራት ማሻሻያ ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህ ዓመት ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚችል ተናግረዋል።

የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ከደረጃ እድገት ጋር በተያያዘ የሚያነሱትን ጥያቄ ለመመለስ እየተሰራ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ካሳሁን፤ ጤና ኬላዎች በቁሳቁስ እንዲሟሉ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።

ዚህ ቀደም ውጤታማ የሆነው የጨቅላ ህጻናት ክትትል እና የቤተሰብ ምጣኔ ስራ በጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲካተት መደረጉንም አስረድተዋል።

የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር መተግበር ከጀመረበት አንስቶ በጤና ዘርፍ የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማሳደግና ግንዛቤ በመፍጠር በበሽታ መከላከል ረገድ የላቀ ውጤት ማምጣቱ ይታወቃል።

ይሀውም በወሊድ ምክንያት የሚፈጠረው የእናቶች ሞት እ.አ.አ. በ1990 ከ100 ሺህ እናቶች 1064 ይሞቱ ከነበረበት በ2016 ወደ 412 የህጻናት ሞት ደግሞ ከ1 ሺህ ህጻናት ይሞቱ ከነበሩት 244 ወደ 67 ዝቅ ማድረግ አስችሏል ።

የመርሃ ግብር ማሻሻያ በማድረግ እየተቀዛቀዘ የመጣውን የጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ማጠናከር እንደሚገባ በመንግስት ታምኖበት በስፋት እየተሰራ ነው።

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እያስመዘገበች ላለው አመርቂ ውጤት የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር ትልቁን ድርሻ ይወስዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም