ኢትዮጵያ የሌሎችን ጥቅም እስካልተጋፋች ድረስ ግድቡን ከመሙላት የሚያግዳት የለም

54

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የሌሎችን ጥቅም እስካልተጋፋች ድረስ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከመሙላት የሚያግዳት እንደማይኖር ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ተናገሩ።

 የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በውሃ የመሙላትና የሙከራ ሥራ ከመጀመሩ በፊት በአገራቱ መካከል ስምምነት መፈረም አለበት ስትል አሜሪካ መግለጫ አውጥታለች።

ይህን አስመልክቶ እንደ ረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ ተደራዳሪና እንደ ዘርፉ ባለሙያነትዎ እንዴት ያዩታል ብሎ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የጠየቃቸው አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ መግለጫው ኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድረው ጫና እንደማይኖር ገልጸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ ወንዝ፣ በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት እየተገነባ ያለና ከኢትዮጵያ የውሃ ድርሻ የሚሞላ ነው።

በመሆኑም ግድቡን የመሙላትም ሆነ ያለመሙላት ውሳኔ የኢትዮጵያ መንግስት እንጂ የሌሎች አካላት ሊሆን አይችሉም ነው ያሉት።

ይህን መሰሉን ጉዳይ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በመግባባት የሚያደርጉት ቢሆን መልካም መሆኑን ገልጸው ፤ ካልሆነም ኢትዮጵያ ግድቡን ከመሙላት የሚያግዳት እንደማይኖር ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያ ሳትስማማበት ምንም ሊያደረግ አይችልም፤ በሌለችበት ግብጽና ሱዳን ስምምነቱን ቢፈርሙ እንኳን የሚያስከትለው ነገር ባለመኖሩ መደናገጥ አይገባም" ብለዋል።

ኢትዮጵያ የላይኛው የአባይ ተፋሰስ አገር እንደመሆኗ ውሃው ያለው እርሷ ዘንድ ነውና፤ ማንም በሃይል ጥቅሟን መጋፋት አይችልም፤ የሌሎችን ጥቅም እስካልተጋፋች ድረስም ግድቡን መሙላት ትችላለች ይላሉ ባለሙያው።

መግለጫው ኢትዮጵያ አደራዳሪዎች ላይ ጥላ የነበረውን እምነት የሚያደበዝዝ መሆኑን ገልጸው፤ አገሪቱ ከዚህ በኋላም የሚያዋጣትን መንገድ መምረጥና ማንም በማይጎዳበት ሁኔታ አካሄዷን ማስቀጠል እንደሚገባት ነው የመከሩት።

ድርድሩ በሌሎች ገለልተኛ አካላት የሚመራበትን መንገድ ማመቻቸትና የዲፕሎማሲ ስራም በሰፊው መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሶስቱ አገራት ውይይቶች ላይ ተሳትፎ የነበራቸው ሌላኛው ባለሙያ ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖም እንዲሁ በግድቡ ዙሪያ ኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ተጽዕኖ ተቀባይነት እንደሌለው ነው የሚናገሩት።

ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ ሉዓላዊ መብቷንና ጥቅሟን የሚያስከብር አሰራር ስትከተል የቆየች አገር ናት አሁንም ይኸው የሚቀጥል ይሆናል ነው ያሉት ዶክተር ያዕቆብ።

ኢትዮጵያ ከሰሞኑ ግድቡን አስመልክቶ ከሱዳን እና ግብጽ ጋር በአሜሪካ በምታደርገው ስብሰባ ላይ እንደማትገኝ ማስታወቋ አይዘነጋም።

በአሁኑ ወቅትም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ለመነጋገር የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድንና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አስቸኳይ ስብሰባ መቀመጣቸው ታውቋል።

ከተጀመረ ዘጠኝ ዓመታትን ያስቆጠረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ70 በመቶ በላይ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም