ኢትዮጵያ ከምዕራባውያኑ ጋር ያላት ግንኙነት በተለያየ ዘርፍ ልምድ እንድታካብት ይረዳታል - ምሁራን

83

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከምዕራባውያኑ ጋር እያደረገች ያለችው ዘርፈ ብዙ ግንኙነት በዴሞክራሲ፣ በህግ የበላይነትና በሰብአዊ መብት መከበር ልምድ የካበተ ልምድ እንድታገኝ ይረዳታል ሲሉ ምሁራን ተናገሩ።

ይሁንና ግንኙነቱ አገሪቱ ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ አሉታዊ ጎኖች እንዳሉትም ነው ምሁራኑ አክለው የሚገልጹት።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በምዕራቡ አለም ከሚገኙ አገራት ጋር ዘርፈ ብዙ ግንኙነት እያደረገች ትገኛለች።

በግንኙነቷም ከተለያዩ የምዕራባውያን አገራት ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ ሌሎች ዘርፈ ብዙ ግንኙነት በማጠናከር የሁለትዮሽ ተጠቃሚነት ለማጠናከር እየሞከረች ነው።

በተለይም ኢንቨስትመንት፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ግብርና፣ የሴቶችና ህጻናት ተጠቃሚነትና ሌሎችም ዘርፎች ኢትዮጵያ ከምዕራባውያኑ ጋር በትብብር የምትሰራባቸው መስኮች ናቸው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ኢትዮጵያ ከምዕራባውያን ጋር ያላት ትብብርና ግንኙነት በተለያዩ መስኮች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለማዳበር የሚረዳ መሆኑን አመልክተዋል።

በኢትዮያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር የሆኑት ዶክተር ምስጋናው ክፈለው እንደገለጹት፤ ግንኙነቱ በተለይም ዴሞክራሲን በማስፈንና የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ ትልቅ ልምድ ይገኝበታል።

የዜጎችን ሰብአዊ መብት በማስከበርና መንግስት ለዜጎች ያለውን ተጠያቂነት እንዲያጠናክርም ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን ዋልታ ረገጥ የሆነ የፖለቲካ ዝንባሌ ለማለዘብም ከምዕራባውያን አገሮች ትምህርት መውሰድ እንደሚቻል ያመለከቱት ዶክተር ምስጋናው፤ ሉዓላዊነትን በማስጠበቅ የሚጠቅሙ ሃሳቦችን መውሰድ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ግንኙነቱ አገር በቀል ሃሳቦችን የመተግበር አቅምን በማይጎዳ መልኩ መተግበር እንዳለበትም አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የልማት ምጣኔ ሃብት መምህር ዶክተር ካሳ ተሻገር በበኩላቸው አገራዊ የኢኮኖሚ ስርዓቱን ግልጽነት በተሞላበት መንገድ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የውጭ አገሮች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖራቸው ትብብር አገር በቀል ኢኮኖሚን እንዳይጎዳ ተገቢ ጥንቃቄ እንደሚፈልግ አመልክተዋል።

ለአብነትም የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ቢፈቀድ ካላቸው አቅም አንጻር የአገር ውስጥ ባንኮችን አቅም ሊፈትን እንደሚችል አንስተዋል።  

ኢትዮጵያ ከምዕራባውያን ጋር ያላት ግንኙነት በቴክኖሎጂ ሽግግርና በሌሎችም መስኮች ልምዶችን ለመቅሰም፣ የተሻለ የንግድ እድል ለመፍጠርና የተለያዩ ብድሮችንና ድጋፎችን ለማግኘት አዎንታዊ ሚና እንዳለው ዶክተር ካሳ አመልክተዋል።

ነገር ግን ግንኙነቱ መርህን የተከተለና በፖሊሲ የተገደቡ ካልሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሃላፊነት ከመጡ ወዲህ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት በብዙ መልኩ መሻሻል አሳይቷል። 

በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ አገሮች በተደረገላቸው ይፋዊ የስራ ጉብኝት ግብዣ እና የተለያዩ አገሮች መሪዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ባደረጉት ይፋዊ የስራ ጉብኝት የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማሳደግና ለማጠናከር የሚያስችሉ ስምምነቶች መደረጋቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም