የፌዴራልና የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች ጉባኤ ተጀመረ

47

ሰመራ ኢዜአ የካቲት 20/2012፡ - አስረኛው የፌዴራልና የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባኤ ዛሬ በሰመራ ከተማ ተጀመረ።
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በጉባኤው መክፈቻ ስነስርዓት ወቅት እንደገለጹት ዜጎች ከየትኛውም የወንጀል ጥቃትና ስጋት ተጠብቀው በሀገራቸው ሰላም ፣ልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ   እንዲሳተፉ ማድረግ ያስፈልጋል።

ለዚህም ጉባኤው በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ያለውን ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ የሚገመግምበት ፣ተምክሮ የሚለዋወጡበትና በጋራ ወንጀልን ለመከላከል የጋራ አቋም የሚያዝበትም መድረክ ጭምር ነው ብለዋል።

በተለይም ቀጣዩ ሀገራዊ ክልላዊ ምርጫ ፍትሃዊና ታአማኒ  ሆኖ ህዝቡ በነጻነት የሚወክለውን እንዲመርጥ ፖሊስ በገለልተኝነት ጸጥታ እንዲያስከብር ተቋማዊ አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

በተለይም የሰው ኃይሉ በጠንካራ ቴክኖሎጂና ፖሊሳዊ ዲሲፕሊን እንዲደራጅ በጉባኤው ማመቻቸት እንደሚገባም አመልክተዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባኤው የ2012  በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት የዘርፉ  የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ይደረጋል።

በተለያዩ ወቅታዊና  ሀገራዊ የጸጥታ ሁኔታዎች ዙሪያ በመምከርም  የጋራ መግባባትና  ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሚያስቀምጥም ይጠበቃል።

በጉባኤው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮች፣ የዘጠኝ ክልሎች እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ፖሊስ ኮሚሽነሮች እየተሳተፉ እንደሚገኙ የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ዋና ሳጂን ኢስሃቅ ሀሰን ገልጸዋል።

ዘጠነኛው የጋራ ኮሚሽነሮች ጉባኤ ባለፈው ዓመት በቢሾፍቱ ከተማ መካሄዱም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም