ወጣቱ ትውልድ የአድዋ ድል የፈጠረው ኢዮጵያዊ አንድነት ሊያስቀጥለው ይገባል --ምሁራን

54

ጎንደር 20/06/2012  (ኢዜአ) ጀግኖች አባቶቻችን በአድዋ ጦርነት የፈጸሙትን የጀግንነት ተጋድሎና ኢትዮጵያዊ አንድነት ወጣቱ ትውልድ የታሪኩ አካል በማድረግ ሊያስቀጠለው እንደሚገባ የጎንደር ዩንቨርሲቲ የታሪክ ምሁራን ገለጹ፡፡

የአድዋ ድል ኢትዮጵያው አንድነትን፣ ጽናትን፣ አይበገሬነትነትን፣ አሸናፊነትንና ነጻነትን ያጎናጸፈ ዘመን ተሻጋሪ ታሪካዊ እለት ነው ያሉት የዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ ትምህርት ክፍል መምህር ግርማ ታያቸው ናቸው፡፡

የአድዋው ድል በባህል፣ በታሪክ፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋና በዘር የተጋመዱ ህዝቦች ቅኝ ገዢና ታስፋፊ የውጪ ወራሪ ጠላትን አንድ ሆነው መክተው በመመለስ ሕያውና አኩሪ ታሪክ የሰሩበት እለት መሆኑን ገልፀዋል።

ወጣቱ ትውልድ ከአድዋው ጦርነት በርካታ አኩሪ የሆኑ ታሪካዊ እሴቶችን ሊማር ይገባል ያሉት መምህር ግርማ ትውልዱ ዛሬ ላይ የተደቀነበትን የመከፋፈል ፈተና ለማለፍ ኢትዮጵያዊ አንድነቱን ሊያጠናክር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በአድዋው ጦርነት አጼ ምኒሊክ ሃይማኖት፣ ጾታ፣ ብሄርና ጎሳ ሳይለዩ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ከጎናቸው በማሳለፍ ለሀገር ሉአላዊነትና ለዳር ድንበራችን መከበር ያደረጉትን ተጋድሎ ወጣቱ ትውልድ ፈለጋቸውን ሊከተል እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡  

የአድዋ ድል የአሸናፊነት ሚስጢሩ ከጫፍ እስከ ጫፍ ኢትዮጵያዊ አንድነት ጎልቶ የወጣበት ታሪካዊ ተጋድሎ በመሆኑ ነው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ ትምህርት ክፍል ሃላፊ መምህር ደሳለኝ ብዙነህ ናቸው፡፡

የአድዋ ድል ከኢትዮጵያውያን አልፎ የመላው ጥቁር ህዝቦች ድል ነው ያሉት መምህር ደሳለኝ "ድሉ አንድ በመሆናችን የተጎናጸፍነው ህዝባዊ ድል ነው" ብለዋል፡፡

በአሉን በየአመቱ መዘከሩና መከበሩ ፋይዳው የጎላ ቢሆንም ከዚህ በዘለለ ትውልዱን በኢትዮጵያዊ አንድነት ቀርጾ በማውጣት በኩል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራትና የሃይማኖት ተቋማት የጎላ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባም አሳስበዋል ።

በሀገራችን የሚስተዋለው የፖለቲካ አለመረጋጋት በህዝቦች መካከል ግጭትና መጠራጠር ብሎም ኢትዮጵያዊ አንድነትን የሚሸረሽሩ አሉታዊ ሁኔታዎች እየፈጠረ በመሆኑ የአድዋን ድል ተምሳሌት አድርጎ ትውልዱን ማነጽ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያውያን ከመቼው ጊዜ በተለየ እርስ በእርሳችን እጅግ አንድነት የሚያስፈልገን ጊዜ ላይ እንገኛለን በማለት የተናገሩት መምህር ደሳለኝ የአድዋው ዓይነት አንድነትና መተባበር አስፈላጊና ወቅታዊ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ልዩነቶች ተፈጥሮአዊ ናቸው አስታርቆና አቻችሎ በመሄድ በአድዋው ጦርነት አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍሰውና ክቡሩ ህይወታቸውን ጭምር ገብረው ያስረከቡንን ሀገር ጠብቆ ማቆየት የትውልዱ ድርብ ሃላፊነት ነው ብለዋል ፡፡   

የአድዋ ድል 124ኛ ዓመት የድል በዓልም በዩኒቨርስቲዎችና በሌሎች ተቋማት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች መከበር ጀምሯል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም