የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች የዋቻሞ ዩኒቨርስቲን ጎበኙ

73

ሆሳዕና፤ የካቲት 20/2012 (ኢዜአ) በሆሳእና ከተማ በስልጠና ላይ የሚገኙ የደቡብ ክልል የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች የዋቻሞ ዩኒቨርስቲን የስራ እንቅስቃሴ ጎበኙ።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ  ለአመራረቹ ስለተቋሙ  የግንባታና ሌሎች እንቅስቅሰዎችን ገለጻ አድርገዋል።

አመራሮቹ ከጎበኙት ውስጥ በ92 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ዘመናዊ የመረጃ ማዕከል ይገኝበታል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁ የተለያዩ ህንፃዎችን፣ የጥናትና ምርምር ማሳለጫ ተቋማትንም ተመልክተዋል።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት  ለመማር ማስተማሩ ስራ ላቅ ያለ አስተዋጽኦ ላደረጉ የሀዲያ ዞን  አመራር  የእውቅና ምስክር ወረቀት ሰጥተዋል።

ከጎብኚዎቹ መካከል የሆሳዕና ከተማ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሻለ ደቦጭ ዩኒቨርስቲው ያስገነባው ዘመናዊ የመረጃ ማዕከል የመማር ማስተማሩን ስራ ለማቀላጠፍ አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተማሪዎችንና የግቢውንም ደህንነት ለማስጠበቅ የተተከለው የደህንነት ካሜራ ለሰላምና ጸጥታ መስፈን የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ለአካባቢው ማህበረሰብ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አጠናክሮ በማስቀጠል ተልዕኮውን ከዳር እንዲያደርስ የአመራሩ ድጋፍ አይለየውም ብለዋል።

ዩንቨርሲቲው በስድስት ማዕከላቱ የምርምር ስራዎችን ተግባራዊ በማድረግ  የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው አመራር ወይዘሮ አጀቡሽ ዋካልቶ ናቸው፡፡

በተለይ በማስተማሪያ ሆስፒታሉ የህክምና አገልግሎት ለማሻሻል እየተሰሩ ያሉት ተግባራት በጤናው ዘርፍ ብቁ የሰው ኃይል ከማፍራት ባሻገር በየደረጃው  ጤንነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

"ዩኒቨርስቲው ተልእኮውን ለማስፈጸም የሁሉም አካል ተሳትፎ ስለሚያስፈልገው እንደ አንድ አመራር የሚጠበቅብኝን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ " ብለዋል።

የደቡብ ክልል ብልጽግ ፓርቲ ተወካይ አቶ ንጉሴ አስረስ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው ከተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያመጣው ለውጥ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

ወቅቱ የሚጠይቀውን ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ስርዓት በመፍጠር የተማሪዎችን ምዝገባ በ"ኦን ላይን"  በማድረግ ጊዜንና የወረቀት ብክነትን ማስቀረት እንደቻለ በጉብኝታቸው ወቅት መረዳታቸውን ተናግረዋል።

ይህም ተልዕኮውን በተገቢው መንገድ ለማስፈጸም ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አመልክተዋል።

በጉብኝቱ ከአንድ ሺህ በላይ  የክልል ብልጽግና ፓርቲ ሰልጣኝ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም