የአድዋ ድል የጥቁር ሕዝቦችን የስነ-ልቦና የበታችነትና የጭቁንነት ስሜት ለውጧል

82

 አዲስ አበባ የካቲት  20/6/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን በአድዋ ጦርነት በኢጣሊያ ላይ ያስመዘገቡት ድል በጥቁር ሕዝቦች ውስጥ የነበረውን የስነ-ልቦና የበታችነትና የጭቁንነት ስሜት የለወጠ እንደሆነ ተገለጸ።

ኢዜአ የአድዋ ድል ለጥቁር ሕዝቦች የፈጠረው የአሸናፊነት መንፈስ ምን ይመስላል? አንድምታውስ ምንድነው? ሲል የታሪክ ምሁርና የጀግኖች አባት አርበኞችን ተወካይ ጠይቋል።

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አልማው ክፍሌ ነጮች በባሪያ ንግድና በቅኝ ግዛት በጥቁር ሕዝቦች ላይ የበታችኝነትና የተሸናፊነት መንፈስ ፈጥረው እንደነበር ይገልጻሉ።

የነበረው የባሪያ ንግድና ቅኝ ግዛትም ጥቁር ሕዝቦች በማንነታቸው እንዳይኮሩ፣ እንዲሸማቀቁና እንዲያፍሩ፤ ነጮች ደግሞ በጥቁሮች ከፍተኛ የንቀት ስሜት እንዲያድርባቸው ማድረጉን ተናግረዋል።

በ1888 ዓ.ም የአድዋ ድል ሲመዘገብ በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች በባርነትና በአገዛዝ ውስጥ እንደነበሩም አውስተዋል።

ኢጣሊያም በወቅቱ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ አሸንፋለሁ በሚል ሰሜት እንደነበረና በጥቁር ሕዝቦች ውስጥ አለ የሚባለው የበታችነት ስሜት እዚህም አለ ብሎ እንደጠበቀ፤ የገጠመው እውነታ ግን የተገላቢጦሽ እንደሆነ ዶክተር አልማው ይናገራሉ።

እናም አድዋ ላይ የተመዘገበው ድል በጥቁር ሕዝቦች ውስጥ የነበረውን የተሸናፊነት ስሜት ቀየረ ይላሉ ዶክተር አልማው።

“በነጮችም ዘንድ ጥቁር የማይረባ ነው፤ ጥቁር አይችልም” የሚለውን ኋላቀር አስተሳሰብም እንደለወጠ ጠቅሰዋል።

የአድዋ ድል በነጮች፣ በጥቁሮችም ሆነ በመላው ዓለም ያለውን ስነ-ልቦና የቀየረ መሆኑንም ተናግረዋል።

የተገኘው ድል ኢትዮጵያዊያን በዓለም እንዲታወቁና አገሪቷም ስሟ እንዲናኝ ትልቅ አስተዋጽኦም አበርክቷል ብለዋል።

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በበኩላቸው “የአድዋ ድል በወቅቱ በቅኝ ግዛት ውስጥ ለነበሩ አገራት ከቅኝ ግዛት መውጣት ይቻላል የሚለውን መንፈስ ፈጥሯል” ይላሉ።

ከአድዋ ድል በኋላ ሌሎች አገራት ከቅኝ ግዛት እየወጡ መምጣታቸውንና ድሉ የአፍሪካ ሕብረት  መቀመጫውን በኢትዮጵያ እንዲያደርግ የራሱን አሻራ ማሳረፉንም ገልጸዋል።

የአድዋ ድል ፍሬ ለጥቁር ሕዝቦች ከፍተኛ የስነ ልቦና መበረታታትና በማንነታቸውና ባላቸው ነገር እንዲኮሩ ማድረጉንም ልጅ ዳንኤል ጆቴ አመልክተዋል።

ድሉ ኢትዮጵዊያን የውስጥ ችግሮችና ልዩነቶች ቢኖሩባቸው እንኳ በአገር ጉዳይ እንደማይደራደሩ ያሳዩበት በመሆኑ አሁን ያለው ትውልድም በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የማያወላውል አቋም እንዲይዝ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑንም አክለዋል።

የፈረንጆቹ የካቲት ወር በአሜሪካ ‘የጥቁሮች ታሪክ ወር’ እየተባለ የሚከበር ሲሆን ወሩ ጥቁር አሜሪካዊያን ለነጻነትና ለመብታቸው ያደረጉት ትግልና ያገኙት ስኬት የሚታወስበት ነው።

የጥቁሮች ታሪክ ወር እንዲከበር ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ዋነኛው የአድዋ ድል ሲሆን ድሉ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትግላቸውን እንዲያጧጡፉ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ይነገራል።

124ኛው የአድዋ ድል በዓል የካቲት 23 ቀን 2012 ዓ.ም በድምቀት ይከበራል።