ኢትዮ-ቴሌኮም የመደበኛ ብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ታሪፍ ቅናሽ አደረገ

61

አዲስ አበባ የካቲት 19/2012 ኢትዮ-ቴሌኮም በመደበኛ ብሮድባንድ ኢንተርኔት ታሪፍ ላይ ከ69 እስከ 72 በመቶ የሚደርስ ቅናሽ አደረገ። 

የመደበኛ ብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ፍጥነቱንም እስከ አራት እጥፍ ማሳደጉን ገልጿል።

የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ ዛሬ የመደበኛ የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ላይ የተደረገውን ማሻሻያ ይፋ አድርገዋል። 

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ኩባንያው ማሻሻያውን ያደረገው ጥራቱን የጠበቀና ተደራሽ የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ለመፍጠር እንደሆነ ገልጸዋል።

አገልግሎቱን የሕብረተሰቡን የመክፈል አቅም ያገናዘበ ከማድረግ ባሻገር ዘርፉን ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ ጭምር መሆኑንም አስረድተዋል።

የታሪፍና የፍጥነት ማሻሻያው ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ሥራ ላይ እንደሚያውልም አክለዋል።

ማሻሻያው ለግለሰቦች፣ ለድርጅቶች እንዲሁም ለድርጅት የቪ.ፒ.ኤን ተጠቃሚዎች ነው የተደረገው።

የድርጅቱ ማርኬቲንግ ኦፊሰር አቶ ኤፍሬም አረፈዓይኔ በበኩላቸው ኩባንያው ለአንድ ሜጋ ባይት ፍጥነት ያስከፍል የነበረውን 978 ብር ወደ 499 ብር ዝቅ አድርጓል።

ለሁለት ሜጋ ባይት ፍጥነት ይጠየቅ የነበረው 1 ሺህ 768 ብር ታሪፍ ወደ 699 ብር፤ 3 ሺህ 191  የነበረው የአራት ሜጋ ባይት ፍጥነት ወደ 1 ሺህ 99 ብር ዝቅ ማለቱንም ገልጸዋል።

ለድርጅት ደንበኞች በወርሃዊ የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ደግሞ እስከ 65 በመቶ የሚደርስ ቅናሽ ማድረጉን አስታውቀዋል።

ለአንድ ሜጋ ባይት ይከፈል የነበረው 1 ሺህ 369 ብር ወደ 709 ብር፤ ለሁለት ሜጋ ባይት ይጠየቅ የነበረው 2 ሺህ 475 ብር ክፍያ ወደ 999 ዝቅ ማለቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ለአራት ሜጋ ባይት ፍጥነት ይከፈል የነበረው 4 ሺህ 468 ብር ደግሞ ወደ 1 ሺህ 575 ብር ቀንሷል ነው ያሉት።

በተመሳሳይ ለድርጅት ደንበኞች የብሮድባንድ ኢንተርኔት ቪ.ፒ.ኤን አገልግሎት እስከ 72 በመቶ ቅናሽ በማድረግ 1 ሺህ 809 ይከፈል የነበረው አንድ ሜጋ ባይት ፍጥነት ወደ 499 ብር ዝቅ ብሏል።

አንዲሁም 2 ሺህ 846 ብር ያስከፍል የነበረው የሁለት ሜጋ ባይት ፍጥነት ወደ 899 ብር፤ 5 ሺህ 137 ብር ያስከፍል የነበረው የአራት ሜጋ ባይት ፍጥነት 1 ሺህ 439 ብር ሆኗል።

ለነባር የባለገመድ ብሮድባንድ ኢንተርኔተ አገልግሎት ደንበኞችም ያለተጨማሪ ክፍያ የአገልግሎት ፍጥነት በሶስት እጥፍ ማደጉን ኦፊሰሩ አብራርተዋል።

ለአዲስ ደንበኞች የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ማስገቢያና ተቀማጭ ገንዘብ ሙሉ ሙሉ የተነሳ ሲሆን፣ ለነባር ደንበኞችም የተቋረጠ አገልግሎት ማስቀጠያ ከክፍያ ነፃ እንዲሆን ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም