የአርሲ ዞንና የአሰላ ከተማ ነዋሪዎች ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል የሚደግፉ መሆናቸውን ገለጹ

84

አዳማ የካቲት 19/2012 (ኢዜአ) በጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ አመራር የመጣውን ለውጥ ከዳር ለማድረስ የሚደግፉ መሆናቸውን የአርሲ ዞንና የአሰላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ከአርሲ ዞን 25 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ነዋሪዎች ዛሬ በአሰላ ከተማ  በመሰባሰብ የድጋፍ ሰልፍ አካሄደዋል።

ከሰልፈኞቹ መካከል በዶዶታ ወረዳ ዴራ ከተማ ነዋሪ ቄስ ሙላቱ ነጋሽ በሰጡት አስተያየት " ዶክተር አብይ አህመድ የአመራር ዘመን ከዚህ በፊት ያልነበረ ነፃነትና ዴሞክራሲ በማግኘታችን ለውጡን ለመደገፍ ነው የመጣነው"  ብለዋል።

የብልፅግናና የመደመር እሳቤን በመደገፍ ሀገርን ለማሻገር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን እንደሚሰለፉ ተናግረዋል።

"ወጣቱ ሰላም ፣ፍቅር፣ ይቅርታና እድገት እንዲደግፍ እሰብካለሁ" ያሉት ቄስ ሙለታ ለውጡ ለውጤት እንዲበቃ ተከታዮቻቸውን ጭምር እያስተማሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

"ሰልፉን ለመታደም የመጣሁት ጠቅላይ ሚኒስትራችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ያመጡትን ለውጥ ከዳር ለማድረስ ያለኝን ድጋፍ ለመግለጽ ነው" ያሉት ደግሞ የአርሲ ዞን ቃድ ሸሪዓ ሼክ ኢሳ ሼክ ሙሐመድ ናቸው።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በተለይ በፖለቲካ ልዩነት ውጭ ተሰደው  የነበሩ ግለሰቦችና የድርጅት ተወካዮች እንዲመለሱና የታሰሩም እንዲፈቱ በማድረግ ሁሉም በሀገሩ ጉዳይ እኩል እንዲወስን ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

የህዝቦች አንድነት ፣መቻቻል፣ ፍቅርና ይቅርታ ዳግም እንዲያብብ እየሰሩ ያሉ መሪ በመሆናቸው ሀገሪቱን ለማሻገር የጀመሩትን የብልፅግና ጉዞ እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

" የህግ የበላይነትን በማጠናከር አስተማማኝ ሰላም እንዲረጋገጥና ቀጣይ ሥራቸው የተሳኩ እንዲሆን እገዛ ለማድረግ ጭምር ነው" ብለዋል።

ወጣት አለሙ ወጋሪ  በበኩሉ ወጣቱ ከአሁን በኋላ የሀገሪቱን የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፍ የድርሻውን መወጣት አለበት ብሏል።

የብልጽግና ጉዞ ከዳር ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል።

የአርሲ ዞን ዋና አስተዳደር አቶ ጀማል አሊይ ህዝቡ ከብልፅግና ጎን ለመቆም በራሱ ተነሳሽነት ያሳየውን ድጋፍ አድንቀው ፤ ልማት፣ ሰላምና አንድነቱን በማጠናከር ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ መረባረብ እንዳለበት አሳስበዋል።

"ብልፅግና ልማት ፣እድገት፣ ዴሞክራሲና አንድነትን የሚያመጣ ነው " ያሉት አቶ ጀማል የዞኑ ህዝብ ይህንን በመደገፍ  ለውጡን ማገዝ እንዳለበት አመልክተዋል።

የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ መንግስት  እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ማንኛውም ተፎካካሪ ፓርቲም ሆነ ግለሰብ ህግን አክብሮ  መንቀሳቀስ እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።

ለብልፅግና ጉዞ ስኬት የአሰላ ከተማና የአርሲ ዞን ነዋሪዎች ከዶክተር አብይ ጎን መቆሙን  በተግባር ማሳየቱን የተናገሩት ደግሞ የአሰላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ገብሬ ዑርጌሶ ናቸው።

ሰላምና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ህዝቡ የድጋፍ ሰልፍ ማድረጉ የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"በከተማዋ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንደ በፊቱ ሁሉ አንድነቱን በመጠበቅ በመቻቻል ፣ በፍቅርና በመሰተሳሰብ ከጎናችን መቆም አለበት" ብለዋል።

በድጋፍ ሰልፉ  ከ80 ሺህ በላይ የሚገመቱ  ነዋሪዎች መሳተፋቸውን ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም