መገናኛ ብዙኃን ለብሔራዊ መግባባት እንጂ ለፖለቲካ ልሂቃን ርዕዮተ ዓለም ማራመጃ እንዳይሆኑ ተጠየቀ

48

አዲስ አበባ የካቲት 19/2012 መገናኛ ብዙኃን ለብሔራዊ መግባባት እንጂ ለፖለቲካ ልሂቃን ርዕዮተ ዓለም ማራመጃ እንዳይሆኑ ተጠየቀ።

የመገናኛ ብዙኃንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን ያሳተፈ በዕርቀ ሠላም እሴቶች ላይ ያተኮረ የሁለት ቀናት ምክክር መድረክ በሠላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

የሠላም ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን ዘመኑ ባለው ፈጣን የመረጃ ልውውጥ ያልተጣሩና ሃሰተኛ መረጃዎች ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ ቀውስ እያስከተሉ መሆኑን ተናግረዋል።

አገር የመገንባትም ሆነ የማፍረስ አቅም ያላቸው መገናኛ ብዙሃኑ ኢትዮጵያ ከመጣችበት የፖለቲካ ሁናቴ አንጻር ከዜጎች ይልቅ ለፖለቲካ ልሂቃን ተዕጽኖ ተጋላጭ እንደሆኑ አንስተዋል።

መገናኛ ብዙሃን በሙያዊ መርሆዎች እየተመሩ ለአብሮነት፣ ለዕርቅ፣ ለፍቅርና ለአገራዊ መግባባት እንጂ ለፖለቲካ ልሂቃን ርዕዮተ ዓለም ማራመጃ መሆን እንደሌላባቸውም ተናግረዋል።

አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ትልቅ አቅምና ጥበብ እንዳለቸው ገልጸው፤ ለብሔራዊ መግባባት ጽንፍ የቆሙ የፖለቲካ ልሂቃንን በማቀራረብ ወደ ምክክር የማምጣት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።

ባለሙያዎች ለህሊናቸው አንዲቆሙና ለህዝብ እውነት ማስተማር ላይ ሊሰሩ ይገባልም ብለዋል።

በሚኒስቴሩ የሠላም ግንባታ ዳይሬክተር ወይዘሮ ራህዋ ሙሴ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያዊያን የጋርዮሽ እሴቶች ላይ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለብሔራዊ መግባባትም በእርቀ ሠላም፣ ታሪክ በማዋሃድና በትናንት የጋርዮሽ ታሪክ ዙሪያ በስፋት ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም