ድርጅቱ የትራንስፖርት አገልግሎቱን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ ተጨማሪ አውቶቡሶችን አስገባ

45

አበባ አበባ ፣የካቲት 19/2012 (ኢዜአ) የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት ድርጅት አገልግሎቱን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ 20 ተጨማሪ አውቶቡሶችን ወደ ስራ ማስገባቱን አስታውቋል።

በርክክቡ ላይ የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ የፌዴራል  እና የአዲስ  አበባ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች  ተገኝተዋል።

በዚሁ ወቅት ሚኒስትሯ አንደተናገሩት፤ የትራስፖርት አገልግሎቱን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ተቋሙ በትኩረት መስራት አለበት።

ወደ ስራ የገቡት አውቶቡሶች "የሰራተኞች መጨናነቅ የሚታይባቸውን መስመሮች በመለየት ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ ናቸው'' ብለዋል ።

አውቶቡሶቹ ጠዋትና ማታ ለሰራተኞቹ አገልግሎት የሚሰጡ ቢሆኑም ከዛ ውጭ ባለው ጊዜ ተጨማሪ አገልግሎት እንደሚሰጡም ጠቅሰዋል።

ከመደበኛ ትራንስፖርት ባለፈ በኪራይ የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጡ አውቶቡሶች በመዲናዋ ያለውን የትራንስፖርት ፍላጎትና አቅርቦት ለማመጣጠን ጉልህ ሚና አላቸው ብለዋል።

በቀጣይ አገልግሎቱን ለአካል ጉዳተኞች ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ አመቺ ሁኔታዎች እንደሚፈጠሩም ጠቁመዋል።

የፐብሊክ ሰርቪስ  ትራንስፖርት ዋና ስራ አስኪያጅ  ወይዘሮ ፍሬህይወት ትልቁ  በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ አገልግሎቱን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ 20 ተጨማሪ አውቶቡሶችን ወደ ስራ አስገብቷል።

በቅርብ ጊዜም ተጨማሪ 30 አውቶቡሶች ወደ  ስራ እንደሚያስገባ ገልጸዋል ።

''ከስድስት ዓመት በፊት  በ50 አውቶብስ አገልግሎቱን  የጀመረው  ተቋሙ  አሁን ላይ 420  አውቶቡሶች ቢኖሩትም ከተጠቃሚው ቁጥር ጋር ሊመጣጠን  አልቻለም'' ብለዋል።

የድርጅቱ ሰራተኞች በሚሰጡት አገልግሎት ደስተኛ ቢሆኑም በአውቶቡሶቹ ቁጥር ማነስ ከፍተኛ መጨናነቅ   በመኖሩ በተለይ ለሴቶች፣ ለአቅመ ደካሞችና ለአካል ጉዳተኞች አስቸጋሪ ሁኔታ መደቀኑን ገልጸዋል።

ድርጅቱ ለቀረበው ቅሬታ ምላሽ ለመስጠት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የጠቀሱት ስራ አስኪያጇ፤ ''በየወቅቱ አገልግሎት የሚያስገባቸው አውቶቡሶች ችግሩን ለመፍታት ለሚያደርገው ጥረት ማሳያ ናቸው'' ብለዋል።

በተጨማሪም ሌሎች አገር በቀል የትራንስፖርት ሰጪ ተቋማት ይህን ፈለግ በመከተል አብረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል ።

አውቶቡሶቹ እጥረት  ባለባቸው በቡራዩ፣ ሰንዳፋ፣ ሆለታ፣ ሰበታና ጫንጮ መስመሮች እንደሚሰማሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም