ሁለት የአዕምሮ ህሙማን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች እየተገነቡ ነው

54

ባህር ዳር  የካቲት 19/2012 (ኢዜአ)  በአማራ ክልል በ275 ሚሊዮን ብር ወጪ ለክልሉ የመጀመሪያ የሆኑ የሁለት ስፔሻላይዝድ የአዕምሮ ህሙማን ማከሚያ ሆስፒታሎች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የጤና መሰረተ-ልማት ግንባታ ሃላፊ አቶ ክንዱ እገዘው ለኢዜአ እንደገለጹት የሆስፒታሎች መገንባት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የአዕምሮ ህሙማን በመደበኛነት ህክምና ለመስጠት ያለመ ነው። 

የሆስፒታሎቹ ግንባታ እየተከናወነ ያለውም በባህር ዳርና ደሴ ከተማ አስተዳደሮች መሆኑን ገልፀዋል። 

ባለፈው ዓመት ግንባታው የተጀመረው የባህርዳሩ ሆስፒታል 20 በመቶ የተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ የደሴ ሆስፒታል ደግሞ በቅርቡ መጀመሩን አስረድተዋል ።

ሆስፒታሎቹ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቁ አቶ ክንዱ ገልፀዋል ።

ሁለቱም ስፔሻላይዝድ የአዕምሮ ህሙማን ማከሚያ ሆስፒታሎች ለአገልግሎት ሲበቁ እያንዳንዳቸው 134 ፅኑ የአዕምሮ ህሙማን ተኝቶ መታከሚያ አልጋዎች ይኖራቸዋል ።

ሆስፒታሎቹ በእነዚህ ከተሞች እንዲገነቡ የተወሰነውም በምዕራብና ምስራቅ አማራ የሚገኙ የችግሩ ተጠቂዎች በአቅራቢያቸው አገልግሎት እንዲያገኙ ታስቦ ነው ተብሏል ። 

እስካሁን ለአዕምሮ ህሙማን የሚሆን እራሱን የቻለ የተደራጀ ሆስፒታል በክልሉ ባለመኖሩ ለአዕምሮ ህሙማን ተገቢውን ህክምና ለመስጠት አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱን የገለፁት ደግሞ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ-ጊዮን  ሪፈራል ሆስፒታል የአዕምሮ ሀኪምና መምህር ዶክተር ሚካኤል በቂ ናቸው። 

እስካሁን እንደ ክልል ለአዕምሮ ህሙማን ታካሚዎች በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱ ታካሚዎች በወረፋ ጥበቃ ጊዜያቸውን ሲያባክኑ በሽታው እየተባባሰ ለከፋ ጉዳት ሲዳርጉ መቆየታቸውን ገልፀዋል ።

የሆስፒታሎቹ መገንባት የአዕምሮ ህሙማንን በተደራጀ አግባብ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ከማስቻል ባለፈ ህሙማን በአጭር ጊዜ እንዲያገግሙ ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል ።

በክልሉ ከ70 በላይ ሆስፒታሎችና ከ800 በላይ ጤና ጣቢያዎች እንደሚገኙም ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም