የመዲናዋ የገቢ ግብር ማሳደጊያ ዕቅድ ይፋ ሆነ

124

አዲስ አበባ የካቲት 19/2012 ( ኢዜአ) በአዲስ አበባ የሚሰበሰበውን ገቢ ግብር ለማሳደግ ሸማቾችን ማዕከል ያደረገ የግብር መሰብሰቢያ ንቅናቄ ይፋ ተደረገ። 

የአዲስ አበባ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን በንቅናቄው ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር ከ15 ቅርንጫፎቹ፣ ከመዲናዋ ምክር ቤትና ከነጋዴዎች ፎረም ጋር የሁለት ቀናት ውይይት ጀምሯል።

ዕቅዱ በአዲስ አበባ ዋነኛ የገቢ ግብር ምንጭ ተብለው ከተለዩት መካከል በዝቅተኛ አፈጻጸም ላይ የሚገኘውን የተጨማሪ እሴት ታክስ ገቢ ግብር ለማሳደግ መዘጋጀቱ ተመልክቷል።

የመዲናዋ ያለፉት ስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸምም ይህንኑ እንደሚያመለክት የባለስልጣኑ ዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ግርማ አስረድተዋል።

በዚህም ከዋና የገቢ ግብር ምንጮች ከኪራይ 110 ነጥብ 63 በመቶ፣ ከደመወዝ 105 ነጥብ 5 በመቶ ገቢ አፈጻጸም ሲመዘገብ፤ ደረሰኝ ከሚቆረጥባቸው ተጨማሪ እሴት ታክስ ገቢ የሚሰበሰበው ግብር ግን 79 ነጥብ 5 በመቶ ነው ብለዋል።    

የባለስልጣኑ የህግ ማስከበር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምራት ንጉሴ ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆን የሸማቹ ደረሰኝ የመጠየቅና የግንዛቤ ማነስ አስተዋጽኦ አድርጓል ይላሉ።

"ሸማቾች ኦዲተሮቻችን ናቸው!" በሚል መሪ ሀሳብ ይፋ የሆነው ዕቅድ በመዲናዋ በሚዘጋጁ የንግድ ባዛሮች አስገዳጅ የደረሰኝ ግብይት ለመተግበር እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

እንደ አቶ ታምራት ገለጻ ደረሰኝ የመቁረጥ ባህል ሸማቾችን ለገዙት እቃ ባለቤት ከማድረጉ ባሻገር ያለ ደረሰኝ ግብይትን ያስቀራል።

የደረሰኝ ግብይት በብዛት በሚስተዋልበት መርካቶ አካባቢ የሚገኙ ቅርንጫፎች ዝቅተኛ ገቢ መሰብሰቡም ተመልክቷል።

ኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማስጨበጥ በመገናኛ ብዙኃንና በንቅናቄው ጥረቱ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

ይህ ዕቅድ የገቢ ግብር አሰባሰቡን ባለቤትነት ለሸማቾች በማጋራትና ሃላፈነታቸውን እንዲወጡ በማድረግ  ባለስልጣኑ የሚያጋጥመውን የሠራተኞች እጥረትም እንደሚያቃልል ተነግሯል።

ባለስልጣኑ ለፍትሃዊ ገቢ አሰባሰብ እንዲያግዘው በተቋሙ ደንብ መሠረት የቋሚ ሠራተኞቹን ንብረት መመዝገቡም ተገልጿል።

ዕቅዱ ከታህሳስ 2012 ዓ.ም ጀምሮ ከባለድርሻ አካላት ጠቃሚ ሀሳቦች እንደተወሰደበት ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም