ከሰባት ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለአበባ ልማት ዝግጁ ሆነ

66
  አዲስ አበባ ሚዝያ 26/2010 በአበባ ልማት ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ከሰባት ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸርና ግብርና ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን አስታወቀ። የመሬት አቅርቦት በበቂ ሁኔታ አለመኖር በኢትዮጵያ የአበባ ልማት ዘርፉ ዋነኛ ማነቆ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ይህም  ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን አቅም እንዳትጠቀም ከማድረግ ባለፈ የሚፈለገውን ያህል የውጭ ምንዛሪ  እንዳታገኝ አድርጓታል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባለፈው ዓመት ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረጉት ውይይት ለአበባ ልማት የሚያስፈልግ መሬት መንግስት እንደሚያቀርብ አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ይታወሳል። በዚሁ መሰረት ከተያዘው በጀት ዓመት መጀመሪያ አንስቶ የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸርና ግብርና ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን ለአበባ ልማት የሚሆን መሬት የመለየት ስራ ማከናወኑን ገልጿል። የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አዱኛ ደበላ ለኢዜአ እንደተናገሩት መንግስት በአበባ ልማት ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ከሰባት ሺህ ሄክታር በላይ መሬት አዘጋጅቷል።  በኦሮሚያ ክልል በአላጌ ግብርና ኮሌጅና በደቡብ ክልል ሻሎ፣ አባያ፣ አርባ ምንጭ፣ ወልቂጤና ይርጋለም፣ በአማራ ክልል ቁንዝላና ብርሸለቆ እንዲሁም በሶማሌ ክልል ሽንሌ ዞን መሬት ተዘጋጅቷል። ባለሙያዎች የውሃና የአፈር ናሙና በመውሰድ የመሬት ተስማሚነት ጥናት አድርገው ቦታዎቹ ለአበባ ልማት ተስማሚ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ብለዋል። ባለሀብቶች የሚያቀርቡት የአዋጪነት የቢዝነስ ዕቅድና በዘርፉ ያላቸው የኢንቨስትመንት ተሞክሮና ፈጥነው ወደ ስራ መግባት መሬቱን ለመስጠት የሚለይባቸው ዋንኛ መስፈርቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። መንግስት በዘርፉ ለመሳተፍ በራሳቸው ገንዘብ መንቀሳቀስ ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ቅድሚያ እንደሚሰጥም ገልጸዋል። በዘርፉ መሰማራት የሚፈልጉና ተሞክሮ ኖሯቸው በቂ ገንዘብ ለሌላቸው የውጭ ባለሀብቶችም 30 በመቶውን ገንዘብ ካቀረቡ ቀሪውን 70 በመቶ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በብድር ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታም ተመቻችቷል ነው ያሉት አቶ አዱኛ። በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጥ ባለሃብቶች በዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ የተሻለ ማበረታቻ እንደሚደረግላቸው አመልክተው 25 በመቶ ገንዘብ ካቀረቡ ቀሪውን በብድር እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል። ባለፈው ሳምንት ከኔዘርላንድስ ባለሀብቶቹ ጋር መሬቱን ተረክበው ወደ ስራ በሚገቡበት ሁኔታ ላይ ውይይት መደረጉን አብራርተዋል። በሌሎችም ስራ ለመጀመር የአገር ውስጥና የውጭ አገር በተለይም የአሜሪካ፣ እስራኤልና ህንድ ባለሀብቶች ፍላጎት ማሳያታቸውን ጠቅሰዋል። ኤምባሲዎችና በቆንስላዎች በኩልም በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የማስተዋወቅ ስራ በእየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል። ከዚህ በፊት በአበባ ልማት የለማው መሬት ከሁለት ሺህ ሄክታር እንደማይበልጥ ያስታወሱት ዶክተር አዱኛ የተዘጋጀው ከሰባት ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ወደ ስራ ሲገባ ኢትዮጵያ ከዘርፉ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንደሚያሳድግ አክለዋል። መሬት የሚወስዱት ባለሀብቶች ስራቸውን በተያዘው ዓመት እንዲጀምሩ ጥረት እንደሚደረግና ለ40 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን አመልክተዋል። ከመሬት ማስተላለፉ ጎን ለጎን የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል። የአበባ ልማት ኢንቨስትመንት 26 በመቶ በአገር ውስጥ ባለሀብቶች፣ 65 በመቶ በውጭ ባለሀብቶች የተያዘ ሲሆን ቀሪው በሽርክና የሚካሔድ መሆኑን ከኢትዮጵያ ሆርቲካልቸርና ግብርና ኢንቨስትመንት ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም