የአውሮፓ ህብረት የኢትዮ-ኬንያ የድንበር ልማትን ይደግፋል ... የአውሮፓ ህብረት

115

የካቲት 19/2012 (ኢዜአ) በአትዮጵያና ኬንያ ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦች መሀከል ከውስን የተፈጥሮ ሃብት መኖር ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማስቀረት የሚካሄደውን ልማት እንደሚደግፍ የአውሮፓ ህብረት ገልጿል፡፡

በኬንያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሲሞን ሞሩዴ ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው በኬንያ የአትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም ጋር ባደረጉት ውይይት በድንበር አካባቢ ከውሃና ከግጦሽ ሳር ባለቤትነት ጋር በተያያዘ ያለውን ግጭት አማራጭ የገቢ ምንጭ በመፍጠር ለመፍታት ተቋማቸው እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ ቀንድ ትስስር እንዲጠናከር ምሁራንን እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኞችን ለማሳተፍ የሚደረገውን ጥረት ድርጅቱ ይደግፋል ብለዋል፡፡

አምባሳደር መለስ ዓለም በበኩላቸው ኢትዮጵያ በምርጫ ዋዜማ ላይ እንደሆነች በመጥቀስ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ መስጠታቸውን በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ኤምባሲው ከካኩማ እና ዳዳብ ስደተኞችን ወደ አገራቸው ለመመለስ እንዲሁም በአገር ቤት ለማቋቋም የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍ ህብረቱ አጋርነቱን እንዲያሳይም ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም