ለችግሮች የመፍትሄ አካል ለመሆን ስልጣንን ለአዳዲስ አመራር ማሸጋገር ተገቢ ነው--- በሚዛን አማንና አርባምንጭ ከተሞች ነዋሪዎች

70
ሚዛን/አርባምንጭ ሰኔ 21/2010 የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስና ለተፈጠሩ ግጭቶች የመፍትሄ አካል ለመሆን  ስልጣን  ለአዳዲስ አመራር ማሸጋገር ተገቢ መሆኑን በሚዛን አማንና በአርባምንጭ ከተሞች ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ በሚዛን አማን  የአዲስ ከተማ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጌታሁን ሻዎ ለኢዜአ እንዳሉት የመንግስት አመራሮች በራሳቸው ፈቃድ ስልጣንን የመልቀቅ ልምድ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት የሃገሪቱን አንድነት በጽኑ መሰረት ለመገንባት አዳዲስ አመራሮችን ወደ ኃላፊነት  ማምጣቱ ተገቢ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ስልጣን በሚለቁ ተተኪ አመራሮችም ከነባሮቹ የተሻሉና ወቅታዊ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል የአመራርነት አቅም ሊኖራቸው እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡ እንደ አቶ ጌታሁን ገላጻ  ሃገሪቱ ካለችበት ወቅታዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ጋር አብሮ በመራመድ  ኃላፊነቱን የሚጣ መሆን አለበት ብለዋል፡፡ የደኢህዴን ሊቀመንበር ከስልጣን በገዛ ፈቃዳቸው ለመልቀቅ መሰረታዊ ምክንያቶች ናቸው ያሏቸው ነጥቦችም ተለይተው ተገቢ መፍትሄ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ " በአሁኑ ወቅት በክልሉ የተከሰተው ግጭትን  አፋጣኝ መፍትሄ  የሚሰጡ አዳዲስ አመራሮች ያስፈልጋሉ"  ያሉት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ አቶ በለው ሰለሞን ናቸው፡፡ የህዝቡን ፍላጎት በተገቢው ተረድቶ ምላሽ ለመስጠትና ለውጥ ለማምጣት የስልጣን ቅብብሎሹ አስፈላጊ ነው፡፡ የስልጣን መተካካቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አቢይ አህመድ ሃገራዊ አንድነትን ለማምጣት እያረጉት ያለውን ጥረት እንደሚያግዝም ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩል የአርባ ምንጭ ነዋሪ አቶ ተስፋለም ባቤና በሰጡት አሰተያየት በክልሉ ባለው  የመልካም አስተዳደርና ኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ግጭቶች እየተስተዋሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ " ሞጋች ህብረተሰብ እየተፈጠረ በመሆኑ የደኢህዴን ሊቀመንበር የነበሩት የተፈጠሩ ችግሮች ሳይባባሱ የመፍትሄ አካል ለመሆን መወሰናቸው ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ነው"ብለዋል፡፡ በእሳቸው የተተኩት ሊቀመንበር የመልካም አስተዳደርና የስራ አጥነት ችግሮችን በተደራጀ መንገድ መፍታት እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል፡፡ በክልሉ ከ56 በላይ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚገኝባት ክልል እንደመሆኑ ይህንን ብዝሃነት በአግባቡ ማስተናገድ ካልተቻለ ችግሩ የከፋ ሊሆን እንደሚችል የተናገሩት ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ማስረሻ ዘውዴ ፡፡ " አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ችግሩ በአዲስ አመራር ሊፈታ እንደሚችል በማሰብ ስልጣናቸውን በገዛ ፍቃዳቸዉ መልቀቃቸው ተገቢ ውሳኔ ነው" ብለዋል፡፡ አክለውም  ከክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የህዝብ ጥያቄዎችን በማጥናት አፋጣኝ ምላሽ ያስፈልጋል፡፡ አዲሱ አመራር የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ፈለግ በመከተል በታችኛው መዋቅር የሚስተዋሉ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ለማስቀረት መታገል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም