በትግራይ የኤች አይ ቪ/ኤዲስ ስርጭትን ለመቆጣጠር ቅንጅታዊ ስራ እንደሚያስፈልግ ተገለፀ

85
መቀሌ ሰኔ 21/2010 በትግራይ የኤች አይ ቪ/ኤዲስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተጀመረው ቅንጅታዊ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ። በቢሮ የኤች አይ ቪ/ኤዲስ መከላከያና መቆጣጠሪያ የስራ ሂደት የማህበራዊ  ንቅናቄ ባለሙያ ሲስተር ሲዒዳ ሳሊህ እንዳሉት በክልሉ የኤች አይቪ/ኤዲስ ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እየተሰራ ቢሆንም በሽታው  አሁንም በወረርሽን ደረጃ ላይ ይገኛል። ክልሉ በቫይረሱ የስርጭት መጠን በሃገር አቀፍ ደረጃ ከአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ሐረርና አፋር ክልሎች ቀጥሎ በአምስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ባለፉት አመታት በተካሄደ ሁለንተናዊ ጥረት ቀንሶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ በክልሉ በተፈጠረው የአመራር እርካታና መዘናጋት ምክንያት ስርጭቱ ዳግም በማገርሸት ወደ 2 በመቶ ከፍ ብሎ እንደነበር ገልፀዋል። እንደገና በሽታውን ለመግታት በተፈጠረው መነሳሳትና መነቃቃት አሁን የስርጭት መጠኑን ወደ 1 ነጥብ 2 በመቶ ዝቅ ማድረግ ቢቻልም ውጤቱ ክልሉ አሁንም በወረርሽኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አመላካች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በክልሉ በአሁኑ ሰዓት 64 ሺህ 800 የሚጠጉ ሰዎች በደማቸው ውስጥ ቫይረሱ እንዳለባቸውና ከመካከላቸውም ከ6 ሺህ በላይ ህጻናት መሆናቸውን ተናግረዋል። ''በደማቸው ውስጥ ቫይረሱ የሚገኙባቸው ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው'' ያሉት ባለሙያዋ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት አሁንም ቅንጅታዊ ስራው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ በተለይ በክልሉ የሚገኙ የሚድያ ተቋማት ጋዜጠኞችና ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ አመልክተዋል። የክልሉ ጤና ቢሮም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በባለቤትነት መስራትና ማስተባበር እንደሚገባው ነው የገለጹት ሲስተር ሲዒዳ። በክልሉ በሚገኙ የሚድያ ተቋማት ከሚሰሩ ጋዜጠኞች መካከል የመቀሌ 104.4 ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ጋዜጠኛ ሽሙዬ ረብሶ እንዳለው ስርጭቱን ለመግታት የሚጠበቅበትን የሙያ ግዴታ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል፡፡ የክልሉ ጤና ቢሮና የሚመለከታቸው ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ስርጭቱን ለመግታት ለሚደረግ ጥረት ድጋፋቸውን ሊያሳዩ እንደሚገባ ጠቁሟል። የትግራይ ክልል የመገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ ባልደርባ ጋዜጠኛ ሄለን በርሄ በበኩሏ በክልሉ የታየውን መዘናጋት ለመስበር የሚድያ ተቋማት  ድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልፃለች። የትግራይ ክልል የኮንስትራክሽን መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወልደአማኑኤል  ገብረ እየሱስ በበኩላቸው ቢሮው በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣት ሰራተኞች ያሉት በመሆኑ በሽታውን አስመልክቶ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይ ለበሽታው ተጋላጭ በሆኑ ኮንስትራክሽና መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ሰራተኞች ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየሰጠ ነው። የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ግንባር ቀደም ሚና ላላቸው ወጣቶች የግንዛቤ ማሳደጊያ ትምህርት እየሰጠ መሆኑን ያስታወቁት ደግሞ የትግራይ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ገብረማሪያም ዘሚካኤል ናቸው። የኤችአይቪ/ኤድስ በሽታ ወረርሽኝ ነው የሚባለው ስርጭቱ ከአንድ በመቶ በላይ ሲሆን እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም