የእህት ከተሞች ግንኙነት ለጎንደር እድገት ያግዛል

100

ጎንደር፣  የካቲት 19/2012 (ኢዜአ) ጎንደር ከተማና የእስራኤልዋ "በሪቨን ለጽዮን" ከተማ የፈጠሩትን የእህትማማችነት ግንኙነት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑን የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ገለፁ ፡፡

በተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ኢንጂነር ማስተዋል ስዩም የተመራ የልኡካን ቡድን ለአንድ ሳምንት በእስራኤል ያደረገውን ጉብኝት አጠናቆ ተመልሷል፡፡

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጉዞውን አስመልክተውበሰጡት መግለጫ ሁለቱ እህት ከተሞች በትምህርት፣ በጤና፣

 በቱሪዝም፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ተደርሷል።

እስራኤል በትምህርቱ ዘርፍ ያላትን የዳበረ ልምድና እውቀት በማካፈል በኩል የጎንደር ከተማን ትምህርት ቤቶች ደረጃ ለማሻሻልና የትምህርት ጥራቱንም ለማረጋገጥ በሚያግዙ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ይሰራል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ  ሆስፒታልን የህክምና ባለሙያዎች አቅም በመገንባት እንዲሁም በዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎች በማደራጀትና በመድሃኒት አቅርቦት በመደገፍ የተሻለ የህክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተደርጓል ።

እስራኤልና ኢትዮጵያ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነታቸው በማደስ በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ትብብራቸውን ማጠናከር እንዲቻልም በጎንደር ከተማ የቤተ-እስራኤላውያን ሙዚየም እንደሚገነባ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

የእህት ከተሞቹን ግንኙነት ለማጠናከር እንዲቻልም በጎንደር ከተማና ዙሪያው የሚገኙ 6 ጥንታዊ የቤተ-እስራኤላውያን የመቃብር ስፍራና የጸሎት ቦታ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

የጎንደርን የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን በእስራኤል ለማስተዋወቅ እንዲቻል በእስራኤል እህት ከተማ በሚገኝ ፓርክ 500 ካሬ ሜትር ቦታ በጎንደር ከተማ ስም መሰጠቱንና ልኡኩ የመታሰቢያ ችግኝ በስፍራው መትከሉን ተናግረዋል፡፡

በወጣቶች የስራ እድል ፈጠራም የእስራኤልን የእህት ከተማ መልካም ተሞክሮ ለመቀመርና ከጎንደር ከተማ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተግባራዊ ለማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የጋራ መግባባት ተደርሷል፡፡

በከተማ መልሶ ማልማትና የፖሊስ ሃይልን የከተማ ጸጥታ አጠባበቅ ስራ በቴክኖሎጂ ለመደገፍ በሚቻልበት ሁኔታም ከእስራኤል እህት ከተማ ጋር የልምድ ልውውጥ መካሄዱን ገልጸዋል፡፡

የልኡካን ቡድኑ የእስራኤልን ወጣቶች የፓርላማ ምክር ቤትን ጨምሮ የተለያዩ ታሪካዊ ስፍራዎችን ከመጎብኘቱም  በላይ ከተለያዩ የአለም ሀገራት ከመጡ የከተማ ከንቲባዎች ጋር የልምድ ልውውጥ ማካሄዱን አብራርተዋል።

በእስራኤል ከሚገኙ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ጋር ውይይት በማካሄድ በጎንደር ከተማ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሰማሩ ጥሪ መቅረቡንም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡      

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም