የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በሰላም እየተከታተሉ ነው

162

ነቀምቴ፣ የካቲት 18/2012 (ኢዜአ ) አያለ ምንም የጸጥታ ችግር ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆናቸውን አንዳንድ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናገሩ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የ3ኛ ዓመት የጂኦግራፊ ትምህርት ክፍል ተማሪ አገሬ በዛብህ በሰጠችው አስተያየት በዩኒቨርሲቲው የጥበቃ ሁኔታ የተጠናከረና የመማር ማስተማሩ ሥራም በጥሩ ሁኔታ ላይ መገኘቱን ተናግራለች፡፡

የባከኑ የትምህርት ክፍለ ጊዜያትም በማካካሻ ፕሮግራም እየተማሩ ሲሆን በተጨማሪም የተየሴሚስቴር አጋማሽ ፈተናም እየተፈኑ መሆናቸውን ገልፃለች፡፡

በዚሁ ትምርት ክፍል ተማሪ ግርማ ሙጨ በዩኒቨርሲቲው የሚያሰጋ የሰላም ችግር ባለመኖሩ ማታ ማታ በቤተመፃሕፍት ጊዜውን እያሳለፈ መገኘቱን ገልጾ ያልተመለሱ ተማሪዎችም ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ ጥሪ አድርጓል።

በዩኒቨርሲቲው ሰላም በመኖሩ ትምህርታቸውን ተከታትለው የሴሚስተር አጋማሽ ፈተና ጨርሰው ለሴሚስተር ፈተና እየተዘጋጁ መሆናቸውን የተናገረችው ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የ2ኛ ዓመት የሕግ ተማሪ ቃል ኪዳን ካሣ ናት፡፡

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ቡሊ ዮሐንስ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው የተረጋጋ ሠላም በመኖሩ የመማር ማስተማሩ ሥራ በጥሩ ሁኔታ መቀጠሉን አመልክተዋል፡፡

የባከኑ የትምህርት ክፍለ ጊዜያትን ቅዳሜና ሕሁድን ጨምሮ በሳምንት ፕሮግራም በማካካስ ተማሪዎችን ለማብቃት ዩኒቨርሲቲው በሙሉ አቅሙ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልጸው ዘገይቶ ወደ ትምርታቸው የተመለሱት ተማሪዎችን በመርዳት እንዲሁም ያልመጡ ተማሪዎችን ለማስተናገድም ዩኒቨርሲቲው ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ በመማር ማስተማሩ ሥራ ላይ አሉታዊ ተጽህኖ መፍጠሩን ገልጸው ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከተው ጋር እየተነጋገሩ መገኘታቸውንም ገልጸዋል፡፡