በጎንደር ከተማ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈበትን መድሃኒት ሲያዘዋውሩ የነበሩ ግለሰቦች ተያዙ

152

ጎንደር የካቲት 18/2012 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን መድሃኒቶች በአንድ ትምህርት ቤት ሲያሰራጩ የተገኙ 15 ግለሰቦችን መያዙን ፖሊስ አስታወቀ።

የከተማው 3ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ደሳለኝ አበራ ለኢዜአ እንደተናገሩት ትናንት ከቀኑ 8 ሰአት መድሃኒቶቹን ሲያዘዋውሩ ከተያዙት ግለሰቦች መካከል 13ቱ የውጭ ሃገር ዜግነት ያላቸው ሲሆኑ ሁለቱ ኢትዮጵያዊያን ናቸው።

ተጠርጣሪዎቹ ምንም ዓይነት የህክምና ፈቃድ እንደሌላቸው ገልጸው በማራኪ ክፍለ ከተማ ልኡል አለማየሁ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚገኙ ተማሪዎች የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን መድሃኒቶች ሲያሰራጩ እንደተያዙም አስረድተዋል።

ፖሊስ ከህዝብ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ባደረገው ክትትል ግለሰቦቹ በትምህርት ቤቶቹ ለሚገኙ 20 ተማሪዎች ያሰራጯቸውን ከሁለት እስከ 10 አመት የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን መድሃኒቶችም መያዝ ተችሏል።

በአንድ የጥርስ መንቀያ መሳሪያና በአንድ መርፌ በርካታ ህጻናት ተማሪዎችን ጥርስ ሲነቅሉና ሲያክሙ መያዛቸውንም ገልጸዋል።

በተለያዩ ግለሰብና ድርጅቶች ስም ይንቀሳቀሱ እንደነበሩ የተገመቱት የውጭ ሃገር ዜጎቹ እስከ አሁን ያዘዋወሩት መድሃኒት መጠንና ያደረሱት ጥፋት እየተጣራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ፖሊስ የጤናና የመስተዳደር አካላት የተሳተፉበት ግብረሃይል በማቋቋሙ የመድሃኒቶቹን ምንነትና የግለሰቦቹን ዝርዝር ሁኔታ በማጣራት ለህዝብ እንደሚገለጽ ዋና ኢንስፔክተሩ አስታውቀዋል።