በድንጋይ መደርመስ አደጋ የሁለት ሰዎች ህይወት አለፈ

119

ሀዋሳ  የካቲት 18/2012 (ኢዜአ) በሀዋሳ ከተማ የድንጋይ ማምረቻ ካብ ተደርምሶ ሁለት ሰዎች መሞታቸውንና በሶስት ሰዎች ላይ ደግሞ መጠነኛ የአካል ጉዳት መድረሱን ፖሊስ ገለፀ ፡፡

የሀዋሳ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ኢዮብ አቤቶ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው ዛሬ ከረፋዱ 5 ሰዓት አካባቢ ላይ  ነው ፡፡

በከተማዋ ሀቤላ ወንዶ ቀበሌ የሚገኘው የድንጋይ ማምረቻ ካብ በመደርመሱ ድንጋይ በማውጣት ላይ ከነበሩት መካከል የሁለቱ ሰዎች ሕይወት ወዲያውኑ ማለፉን ተናግረዋል።

መጠነኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሌሎች ሶስት ሰዎች ደግሞ በሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል ብለዋል ፡፡

በሰዎች ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ ካባው ውስጥ በሥራ ላይ የነበረ “ ኤክስካቬተር ” ማሽን ላይ ጉዳት መድረሱንም ጠቁመዋል ፡፡

በከተማዋ ባሉ የድንጋይ ማዕድን ማውጫ ስፍራዎችም ሆነ በአንዳንድ የግንባታ ሥራዎች ላይ የሚሰማሩ ሰራተኞች የጥንቃቄ አልባሳትና ቁሳቁሶችን ያለመጠቀም እንዲሁም ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችን አስቀድሞ ያለመቀነስ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል ፡፡

አሰሪዎች ለሰራተኞች አስፈላጊውን ቁሳቁስ የማሟላት እንዲሁም የመስሪያ ቦታዎች ከአደጋ ሥጋት የፀዱ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል ።

በቀጣይም የከተማዋ ፖሊስ በዚህ ረገድ ያሉት ችግሮች እንዲቀረፉ አስፈላጊውን የእርምት እርምጃና ሕግን የማስከበር ተግባር እንደሚሰራ አዛዡ ገልፀዋል፡፡