ዩኒየኑ የህብረተሰቡን የዳቦ ዱቄት ፍላጎት ለማሟላት እየሰራ ነው

59

ማይጨው፣ የካቲት 18/2012 (ኢዜአ) ቦክራ የአርሶ አደሮች ህብረት ስራ ዩኒየን አርሶ አደሩ የሚያመርተው ስንዴ በግብአትነት በመጠቀም የህብረተሰቡን የዳቦ ዱቄት ፍላጎት ለማሟላት እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

ማይጨው የሚገኘው ቦኽራ የህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየን ዋና ስራአስኪያጅ አቶ አታክልቲ ከበደ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒየኑ በ7 ነጥብ 6 ሚልዮን ብር ያቋቋመው የዳቦ ዱቄት ፋብሪካ የማምረት ስራ ጀምሯል።

ዩኒየኑ ከውጭ በድጎማ የሚመጣውን ስንዴ ሳይሆን በትግራይ ደቡባዊ ዞን ስንዴ አብቃይ የሆኑ የአርሶ አደሩን የስንዴ  ምርት በመጠቀም የህብረተሰቡን የዳቦ ዱቄት ፍላጎት ለሟሟላት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።


ፋብሪካው ከአካባቢው አርሶ አደሮች የሚያመርቱትን ስንዴ በመጠቀም በቀን 420 ኩንታል የዳቦ ዱቄት ማምረት መጀመሩን ተናግረዋል።

 የፋብሪካ የማምረት ስራ መጀመር አርሶ አደሩ ገበያ ተኮር የሆነ ምርት ለማምረት እንደሚያነሳሳውም ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

ዩንየኑ ከአካባቢው መልክአ ምድር ተስማሚ የሆኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶአደሩ በማቅረብ የተሻለ የስንዴ ምርት እንዲመረት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የድህረ ምርት ብክነት ለመከላከልም ኮምባይነር እና ሌሎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ የተሻለ ምርት እንዲያገኝና ተጠቃሚ እንዲሆን የማድረግ ስራ ይከናወናል።

ዩኒየኑ ከውጪ የሚመጣውን ስንዴ በማስቀረት የህብረተሰቡን የዱቄት ፍላጎት ለማሟላት እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑንም ስራአስክያጁ ተናግረዋል።


በእንዳመኾኒ ወረዳ የመካን ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ባይሩ ሐጎስ በሰጡት አስተያየት የፋብሪካው ስራ መጀመር አርሶ አደሩ ገበያ መሰረት እድርጎ እንዲያመርት  ያግዛል ብለዋል።

ከዚህ በፊት ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የመጠቀም ባህላችን ደካማ ስለነበር ከአንድ ጥማድ መሬት ሲገኝ የነበረው ምርት ከስምንት ኩንታል ስንዴ የዘለለ አልነበረም በማለት ገልፀዋል።

አሁን ግን በትራክተር ማረስ በመጀመራችንና የማዳበሪያ አጠቃቀማችን በመሻሻሉ ከተመሳሳይ መሬት 14 ኩንታል ስንዴ ማምረት ጀምረናል ብለዋል።

 ዘመናዊ የእርሻ አተራረስ ዘዴው በቂ የስንዴ ምርት ለፋብሪካው ለማቅረብ አመቺ መሆኑን ገልጸዋል።

ፋብሪካው ስራ መጀመሩን ተከትሎ ከስምረት ቀበሌ  ብቻ ለዱቄት ፋብሪካው ግብአት የሚሆን ከ300 ኩንታል በላይ ስንዴ በሽያጭ ማቅረባቸውን የተናገሩት ደግሞ አርሶ አደር ወልደገብርኤል ሽሙየ ናቸው።

ከዚህ በፊት ያመረትነው ስንዴ ወደ ገበያ ለማድረስ በኩንታል ለትራንስፖርት 40 ብር ለመክፈል እንገደድ ነበር ያሉት አርሶ አደሩ አሁን ግን ፋብሪካው በራሱ ትራንስፖርት ስለሚያጓጉዘው ጊዜና ገንዘብ እንደቆጠበላቸው ተናግረዋል።

በትግራይ ደቡባዊ ዞን ከ36 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በስንዴ የሚሸፈን መሆኑን ከዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም