የተቋማቱ በጎ ምላሽ 200 ሕሙማን ነፃ የኩላሊት እጥበት ሕክምና እንዲያገኙ አስችሏል

80

 አዲስ አበባ የካቲት 18 /2012 (ኢዜአ) የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ለተቋማት ስራ አስኪያጆች ባቀረበው ጥሪ በተገኘ ምላሽ 200 የኩላሊት ሕሙማን ነፃ የእጥበት አገልግሎት ማግኘት ችለዋል። 

ጥሪውን ተከትሎ 16 ድርጅቶች ድጋፍ ማድረግ በመጀመራቸው ከሕሙማኑ በዓመት ይጠበቅ የነበረውን ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ መሸፈን ተችሏል።

የነፃ አገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ ታካሚዎችም የሚደረግላቸው ድጋፍ የነበረባቸውን ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ ጫና እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል።

አብርሃም ማሞ የኩላሊት ሕመም የጀመረው የዛሬ አራት ዓመት ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለመመረቅ አንድ ወር ሲቀረው ነበር። 

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኩላሊት እጥበት /ዲያሊሲስ/ እያደረገ መቆየቱን የሚናገረው አብርሃም ለአምስት ወራት በራሱ ወጪ፣ ከሶስት ዓመት በላይ ደግሞ በቢጂአይ ኢትዮጵያ ድጋፍ መጠቀሙን ገልጿል። 

"ዲያለሲስ ስለሚያደክም ሶስት ቀን እታጠባለሁ ሶስት ቀን ቤቴ ነው የማርፈው" ያለው አብርሃም ዘመድ ጋር ተጠግቶ እንደሚኖር የተናገረው። 

የራሱ ገቢ ስለሌለውና የቤተሰቡም አቅም ህክምናውን ማድረግ የሚያስችል ባለመሆኑ ድርጅቱ ወጪውን ባይሸፍንለት በሕይወት መኖሩ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ መሆኑንም ተናግሯል።

አቶ ፋንታሁን መሀመድ ደግሞ የኩላሊት እጥበት ወጪያቸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ድጋፍ  መሸፈኑን ይናገራሉ። 

ከአፋር ክልል የመጣችው ነስራ ብርሃኔም ለስድስት ዓመታት ዲያሊሲስ ስታደርግ መቆየቷን ትናገራለች፤ ሌሎች ድርጅቶችም በመሰል በጎ ተግባራት እንዲሰማሩ ተማጽኖዋን አቅርባለች።

የኩላሊት ሕሙማን ከዲያሊሲስ በተጨማሪ የመድሃኒትና ሌሎችም ወጪዎች እንዳሉባቸው በመረዳት ድርጅቶቹ ድጋፍ እንዲያደርጉም ነው የጠየቁት። 

የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ ለኢዜአ እንዳሉት ድርጅቱ ላለፉት ስምንት ዓመታት የኩላሊት እጥበት አገልግሎት በአገር ውስጥ በስፋት እንዲሰጥና የኀብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ሲሰራ ቆይቷል።

የኩላሊት እጥበት ወጪ በታካሚዎችና ቤተሰቦቻቸው ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስና ሕሙማኑ አገልግሎቱን በነፃ እንዲያገኙ ለማድረግ ለተቋማት ስራ አስኪያጆች ጥሪ ማስተላለፉን አውስተዋል። 

ጥሪውን ተከትሎ ቀደም ሲል ለሕሙማን ድጋፍ ሲያደርግ የቆየው ቢጂአይ ኢትዮጵያ ድጋፉን በማኅበሩ በኩል ማድረጉንና 16 ተቋማት ድጋፍ ማድረግ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በቅርቡም ድጋፍ ለማድረግ የተዘጋጁ የግልና የመንግስት ተቋማት መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በዘውዲቱና በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታሎችና በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የኩላሊት እጥበት ሲያደርጉ ለነበሩ ታካሚዎች አገልግሎቱን ለአንድ ዓመት በነፃ እንዲያገኙ ወጪያቸውን መሸፈኑን አስታውሰዋል። 

ከተማ አስተዳደሩ በእነዚህ ሆስፒታሎች ያሉ ታካሚዎችን ወጪ መሸፈኑን ተከትሎም ድርጅቱ ሕክምናቸውን በግል እየተከታተሉ ላሉ ሕሙማን ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል። 

ከአንድ ሺህ በላይ ሕሙማን ድጋፉን እየተጠባበቁ መሆኑን ያነሱት አቶ ሰለሞን "ስራ አስኪያጆች ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም ለተቀሩት እንድንደርስላቸው ይደግፉን” ሲሉ ጠይቀዋል። 

ኀብረተሰቡና አቅም ያላቸው አካላትም የኩላሊት እጥበት እያደረጉ ለሚገኙና ደጋፊ ለሌላቸው ታካሚዎች እንዲደርሱላቸው ጥሪ አቅርበዋል። 

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሳሙኤል ዘሚካኤል አንድ በመንግስት ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት የሚያደርግ ታማሚ በወር በአማካይ እስከ ስድስት ሺህ ብር እንደሚያወጣ ይገልጻሉ።

የከተማ አስተዳደሩ ሕመሙ በታካሚዎች ላይ የሚያደርሰውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ ከ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል። 

በዚህ ድጋፍ በሶስቱ የመንግስት ሆስፒታሎች ከ100 በላይ ሕሙማን ለአንድ ዓመት ነፃ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን በመጥቀስ። 

ለኩላሊት ሕመም የሚያጋልጡትን እንደ የደም ግፊትና ስኳር የመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎች የመከላከል ስራ መጠናከሩንም ዶክተር ሳሙኤል ተናግረዋል። 

ኅብረተሰቡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ለኩላሊት ሕመም የሚያጋልጡ በሽታዎችን እንዲቆጣጠር ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም