በመቀሌ ከተማ የአረጋዊያን እንክብካቤ ማእከል ተገነባ

104

መቀሌ የካቲት 18/2012 (ኢዜአ) በመቀሌ ከተማ በመንግስትና በባለሃብቶች ድጋፍ የተገነባው የአረጋዊያን ማቆያና እንክብካቤ ማእከል ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን የማእከሉ ስራ አስኪያጅ አስታወቁ።

በትግራይ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማእከሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ ግርማይ እንዳሉት ለሃገራቸው የማይደበዝዝ ታሪክ ሰርተው ለቀጣይ ትውልድ ያስተላለፉት አረጋዊያንን መደገፍ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

 በመቀሌ ከተማ ዓዲሓቂ ክፍለ ከተማ ውስጥ በመንግስትና በግል ባለሃብቶች ድጋፍ በ9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ባለሁለት ዘመናዊ ፎቅ ህንጻ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ 26 ክፍሎች ያሉት ነው።

ማእከሉ ጧሪና ምንም ዓይነት ገቢ የሌላቸውን 261 አረጋዊያን ተቀብሎ ለማስተናገድ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ምልመላ እየተካሄደ በመሆኑ ከአንድ ወር ተኩል በኃላ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል ።

አረጋዊያኑ የሚገለገሉባቸው አልጋዎች ፣ ፍራሾች ፤ አንሶላና ብርድ ልብስ በ1 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ወጪ ግዥ ለመፈጸም በሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በአረጋዊያን ማእከሉ ውስጥ ተጨማሪ 48 ክፍሎች ያላቸው ሁለት ህንፃዎች በቀጣይ ዓመት ለማስገንባት እቅድ ተይዟል ።

በትግራይ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የችግረኛ ማህበረሰብ አቅም ግንባታ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አደራጀው ሺሻይ በበኩላቸው በክልሉ የህብረተሰቡ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ከ100 ሺህ በላይ አረጋዊያን መኖራቸውን ገልጸዋል።

በተገነባውና ለአገልግሎት ዝግጁ በሆነው የአረጋዊያን ማቆያና እንክብካቤ ማእከል ልዩ ኩራት ተሰምቶኛል ያሉት ደግሞ የትግራይ አረጋውያን ማህበር ሊቀመንበር አቶ አርአያ ገሰሰ ናቸው።

በቀጣይ ዓመትም በመንግስትና ባለሃብቶች ትብብር በዓብይ ዓዲና በሁመራ ከተሞች ተመሳሳይ ማእከላት  ለመገንባት የቦታ ርክክብ መፈጸሙን ተናግረዋል።

የሃገር ህልውናና ትውልድ እንዲቀጥል ያደረጉ አረጋዊያን ከያሉበት አካባቢ ሳይፈናቀሉ ተገቢውን እንክብካቤ  እንዲያገኙ ለማድረግ አቅም ያለው ሁሉ ድርሻውን እንዲያበረክትም አቶ አርአያ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም