እየገጠሙን ያሉ አዳዲስ ፈተናዎች ወደ ብልፅግና ከምናደርገው ጉዞ አያስቀሩንም- ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ

114

የካቲት 18/2012(ኢዜአ) እየገጠሙን ያሉ አዳዲስ ፈተናዎች ወደ ብልፅግና ከምናደርገው ጉዞ አያስቆሙንም ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በከንባታ ጠንባሮ ዞን ዱራሜ ስታዲየም ለተሰበሰቡ በሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ንግግር አድርገዋል።

በመልእክታቸውም የከንባታ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በፍቅርና በመተሳሰብ አብሮ በመኖር "መደመርን" ቀድሞ የተረዳ ህዝብ መሆኑን ተናግረዋል።

"አገር ሳትበለፅግ ብቻውን የሚለማና የሚበለፅግ ማህበረሰብ አይኖርም" ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህንን እውን ለማድረግም ኢትዮጵያን ማበልፀግ ቁልፍ አጀንዳችን አድርገን እየሰራን ነው ብለዋል።

በዚህ የብልፅግና ጉዞ እየገጠሙን ያሉ አዳዲስ ፈተናዎች ቢኖሩም ከስኬት ጉዟችን ሊያደናቅፉን አይችሉም ሲሉም አረጋግጠዋል።

በተለይ ወጣቶች ኢትዮጵያን ለማቆም የደም ዋጋ የከፈሉ አባትና እናቶችን ውለታ ለመመለስ ለአገር ብልፅግና በጋራ መስራት እንዳለባቸው መክረዋል።

"የእኔ መስመር ብቻ ትክክለ ነው" የሚል ግትር አስተሳሰብም ለህዝቦች ብልፅግና እና ለኢትዮጵያ አንድነት አይጠቅምም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ በስታዲየም ለታደመው ህዝብ መልእክት ካስተላለፉ በኋላ  ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ጀምረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም