ድርጅቱ ለትምህርትና ስልጠና ተቋማት ስድስት ሚሊዮን ብር የሚገመት ቁሳቁስ ሰጠ

57

አዲስ አበባ፣ የካቲት17/2012 (ኢዜአ) ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት አይ.ኦ.ኤም ለትምህርትና ስልጠና ተቋማት ስድስት ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

የቁሳቁስ ድጋፉ ወደ ውጭ አገራት የሚሄዱ ሠራተኞች እውቀትና ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ያግዛል ተብሏል።

ከቁሳቁሶቹ መካከል ኮምፒዩተሮች፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽን፣ ማቀዝቀዣ፣ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የቡናና ሻይ ማፍያዎችና የፅዳት ዕቃዎች፣ የፍራፍሬ መፍጫ፣ የኤሌክትሪክና የጋዝ ምድጃዎችና ሌሎችም ይገኙበታል።

ድጋፉን ለሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቱ ያስረከቡት የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ የስደት አስተዳደር ፕሮግራም አስተባባሪ ማላቦ ሞንጋ ናቸው።

ቁሳቁሶቹ ከፍተኛ የሰው ፍልሰት በሚታይባቸው አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይና ደቡብ ክልሎች ለሚገኙ 16 የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት እንደሚከፋፈሉ ተገልጿል።

የድርጅቱ ድጋፍ ተቋማቱ ለሚሰጡት የስልጠና አገልግሎት የሚውል ሲሆን ዜጎች በተቋማቱ የሚያገኙት ትምህርት ወደ ውጭ አገራት ሲሄዱ እንዳይቸገሩና አቅማቸውንም እንዲያጎለብቱ እንደሚያግዝ ተገልጿል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ አየለች እሸቱ በውጭ አገራት በቤት ሠራተኝነት የሚቀጠሩ ኢትዮጵያዊያን ሥራቸውን በእውቀትና በክህሎት በመከወን በኩል ክፍተት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

"የቁሳቁስ ድጋፉ ወደውጭ አገራት የሚሄዱ ሠራተኞች ስልጠናና ትምህርት አግኝተው ብቃታቸውን እንዲያሳድጉና ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ ያግዛል" ብለዋል።

የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ የስደት አስተዳደር ፕሮግራም አስተባባሪ ማላቦ ሞንጋ በበኩላቸው የትምህርትና ስልጠና ተቋማቱ የሚሰጡት ስልጠና ሠራተኞች ሙያዊ ብቃት እንዲኖራቸውና በሚሄዱበት አገር ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

በሙያቸው ብቁ የሆኑ ሠራተኞችም መብታቸውን ለማስከበር እንደማይቸገሩ አክለዋል።

አስተባባሪው እንዳሉት ተቋሙ ስደተኞችን አስመልክቶ ለኢትዮጵያ የሚያደርጋቸውን ድጋፎች ይቀጥላል።

ድርጅቱ የቁሳቁስ ድጋፉን ያደረገው የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባቀረበው ጥያቄ መሰረት እንደሆነ በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም