ዩኒየኑ ያስገነባው የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የሙከራ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

122

ሁመራ የካቲት 17/2012 (ኢዜአ) የሁመራ ገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ያስገነባው የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የሙከራ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

የፋብሪካው አስተባባሪ አቶ አስገለ ዘሪሁን እንደገለጹት ፋብሪካው የተገነባው በተያዘው ዓመት ውስጥ አምስት ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ ነው።

ካለፈው ሳምንት አንስቶ ለሙከራ በጀመረው አገልግሎት በቀን 300 ሊትር ወተት በማቀነባበር ለተጠቃሚዎች ለሽያጭ እያቀረበ ነው።

የወተት ምርቱን የሚያገኘው ዩኒየኑ በስሩ ከሚያስተዳድራቸው ማህበራት አባላት በማሰባሰብ እንደሆነ አስተባባሪው አመልክተዋል።

ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ በቀን ከ6 ሺህ ሊትር በላይ ወተት ማቀነባበር ይችላል።

በ5 ሺህ ካሬ መሬት ላይ ያረፈው ፋብሪካ የወተት ተዋፅኦ የሆኑትን እርጎ፣ቅቤ፣እሽግ ወተትና ሌሎች አገልግሎቶችን በማቀነባበር አገልግሎት ይሰጣል።

ምርቶቹን ለውጭ ለማቅረብ እቅድ እንዳለው ያመለከቱት አቶ አስገለ በተለይ በትግራይ ምዕራባዊ ዞን ለሚገኙ እንስሳት አርቢ አርሶ አደሮችና ባለሃብቶች ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

ከአካባቢው አርሶ አደሮች መካከል አቶ ገብረጻድቅ ተክሉ በሰጡት አስተያየት የፋብሪካውን ስራ መጀመር ከሌላው መደበኛ የግብርና ስራቸው በተጓዳኝ የወተት ላሞችን እርባታ ለማካሄድ መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

"ከዚህ ቀደም ከወተት ተዋፅኦ የምናገኘው ጥቅም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም " ያሉት ደግሞ በቃፍታ ሁመራ ወረዳ የራውያን ገጠር ቀበሌ አርሶ አደር ብርሃነ አባይ ናቸው።

የፋብሪካው ስራ መጀመር ከምርቶቻቸው የተሻለ ጥቅም ለማግኘት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።

የሁመራ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን በስሩ ስድስት ማህበራትን እንደሚያስተዳድር ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም