በአዲስ አበባ ታላቁ አንዋር መስጊድ የሴቶች መግቢያ አካባቢ በደረሰው የእሳት አደጋ 50 ሱቆች ተቃጠሉ

133
አዲስ አበባ ሰኔ 21/2010 በታላቁ አንዋር መስጊድ የሴቶች መግቢያ አካባቢ በደረሰው አደጋ ከ50 በላይ ሱቆች መውደማቸውን የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር የህዝብ ክንፍ አብይ ኮሚቴ አስታወቀ። እሳቱ ከሌሊቱ 7 ሰዓት አካባቢ የተነሳ ሲሆን፤ በህብረተሰብ ተሳትፎና የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ  አደጋ መከላከልና መቆጣጠር አካላት እንዲሁም ከአየር መንገድ በመጡ ባለሙያዎች በተደረገው ርብርብ በቁጥጥር ስር ውሏል። የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር የህዝብ ክንፍ አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሃይማኖት አለሙ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት፤ መስጊዱ ከሚያስተዳድራቸው 385 ሱቆች መካከል 50 የሚሆኑት ሱቆች ወድመዋል። በዋናው መስጊድ ላይ ግን ምንም ጉዳት አለመድረሱን ነው ያረጋገጡት አቶ ሃይማኖት። አደጋው በመስጊዱ ውሰጥ ለረዥም ዓመታት የሴቶች የሃይማኖት ትምህርት መማሪያ የነበረ አንድ ቤት ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፤ በሌላ የግል መምህር የሃይማኖት መጻሕፍት ላይ ግን ጉዳት መድረሱ ተገልጿል። በሴቶቹ መማሪያ ቤት ውስጥ የነበሩ የሃይማኖት መጻሕፍት ቀድመው በአካባቢው ወጣቶች በማውጣታቸው ከአደጋው ተርፈዋል። አደጋው በተነሳበት ሰዓትም በአቅራቢያ ያሉት የአራዳና የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የእሳት አደጋ መከላከያና መቆጣጠሪያ አካላት እሳቱን ለማጥፋት ተረባርበዋል። እንደ አቶ ሃይማኖት ገለጻ  ሱቁቹ በኮምፖርሳቶና በቀላል ነገር የተሰሩ መሆናቸው፣ በውስጣቸው ያሉ ተቀጣጣይ ነገሮችና ፕላስቲኮች መብዛታቸው እንዲሁም ቦታው ለእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች አመች ባለመሆኑ እሳቱን በፍጥነት ለማጥፋት አስቸጋሪ አድርጎት እንደነበር ገልጸዋል። አደጋው ያደረሰው የጉዳት መጠንና የአደጋው መንስዔ እየተጣራ መሆኑንም ባለስልጣኑ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም