በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚደረገው ቁጥጥር ተጠናክሮ ቀጥሏል

48

አዲስ አበባ ( ኢዜአ)  የካቲት 17/2012 የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19ን) ለመከላከል ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመሆን እየተከናወነ ያለው የቁጥጥርና የክትትል ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሰታወቀ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድም የተጓዦችን የሙቀት ልየታና የጉዞ ታሪክ በሚመለከት ከኢንስቲትዩቱ ሙያተኞች ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ ለኢዜአ እንደገለጹት በአገር አቀፍ ደረጃ ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል።

በተለይም ከቻይና እና ቫይረሱ ከተከሰተባቸው አገራት የሚመጡ መንገደኞችን የሙቀት መጠናቸውንና የጉዞ ታሪካቸውን በማጣራት አስቀድሞ ለመከላከል ከአየር መንገድ ሳይወጡ በጥብቅ ምርመራ እየተደረገላቸው ነው ብለዋል።

ከጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በሰባቱ መግቢያዎች ከ146 ሺህ 357 በላይ መንገደኞች በሙቀት ልየታው ያለፉ ሲሆን ከነዚህ ውስጥም 3 ሺህ 901 ቫይረሱ መኖሩን ሪፖርተ ካደረጉ አገራት የመጡ ናቸው።


በሁሉም የገሪቱ መግቢያ ጣቢያዎች 248 ሺህ 734 ዜጎች በሙቀት መለያው እንዳለፉና 697 የሚሆኑት ደግሞ ባሉበት ቦታ ሆነው የጤና ክትትል እየተደረገላቸው ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ እስካሁን በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተጠቃ ሰው የለም ብለዋል።

እስካሁን 60 የጥርጣሬ መረጃዎች ለኢንስቲትዩቱ የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል ደርሶ እንደነበር አስታውሰው ፤ በሁሉም ጥቆማዎች ላይ የማጣራትና የቁጥጥር ስራ ተከናውኗል ብለዋል።

ከጥቆማዎቹ መካከል 17ቱ በቫይረሱ ተጠርጥረው ስለነበርና የቻይና የጉዞ ታሪክ ስለነበራቸው በተለያየ ጊዜ በለይቶ ማቆያ ማዕከል እንዲቆዩ ተደርጓል።

በተደረገላቸው ምርመራ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ተረጋግጦ ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል ነው ያሉት።

ለዚህም ደግሞ ኢንስቲትዩቱ ከኢትዮጰያ አየር መንገድ ጋር ጠንካራ የሆነ ቅንጅታዊ አሰራርን ዘርግቶ ወደ ስራ በመግባቱ ቀልጣፋና ውጤታማ ስራን እንዲያከናውን አስችሎታል። 

በአሁኑ ወቅትም ኢኒስቲትዩቱ ቫይረሱን መመርመር የሚያስችል ሙሉ አቅም እንዳለውና ለዚህም በቂ የመመርመሪያ ላብራቶሪ ማእከልና ግብአቶችን ማሟላቱንም ገልጸዋል።

በተለይም የቫይረሱን መከሰት ከተሰማበት ግዜ ጀምሮ በጤና ሚኒስቴርና በኢንስቲትዩቱ አስተባባሪነት ግብረ ሃይል ተቋቁሞ በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገባ ተደርጓል።

በተለይም ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያና በአገሪቱ ባሉ 27 ቦርደሮች ላይ የመንገደኞችን ሙቀት መለየትና የጉዞ ታሪክ ማጣራት ላይ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ።

በአሁኑ ወቅት ከቻይናም ሆነ ቫይረሱ ከተከሰተባቸው ሌሎች አገራት የሚመጡ መንገደኞች ለሶስት ግዜ ያክል የሙቀት ልየታ ምርመራ ይደረግላቸዋል ብለዋል። 

ተግባሩን የሚያከናውኑ ሙያተኞችም ለ24 ሰአታት ዝግጁ ሆነው በአየር መንገዱ ግዜያዊ የምርመራ ማዕከል እንዳሉም አክለዋል።

በተለይም በተጓዞች ላይ አጠራጣሪ ነገሮች ሲስተዋሉ ከአየር መንገዱና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ወደ ለይቶ ማቆያ ማዕከላት በጥንቃቄ እንዲያመሩ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው የሚናገሩት።

የኢትዮጰያ አየር መንገድ በበኩሉ ከኢንሲትቲዩቱ ጋር በቅንጅት እየሰራ ሲሆን ከቻይና የሚመጡ አውሮፕላኖቹን መድሃኒት በመርጨት ቫይረሱን ለመከላከልም በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

በአየር መንገዱ የቱሪዝምና የኢንተርኔት ዲጂታል ሴልስ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ቃኘው ፍሰሃ እንደሚሉት የአለም የጤና ድርጅት በቫይረሱ ዙሪያ የሚያስተላልፈውን መረጃ መነሻ በማድረግ የቁጥጥርና የክትትል ስረአቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በቅደሚያ ማንኛውም መንገደኛ ከቻይና ከመነሳቱ በፊት እዛው እያለ የቫይረሱ ምርመራ እንደሚደረግለት አረጋግጠዋል።

መንገደኞችን አሳፍሮ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የደረሰው አውሮፕላንም ከሌሎች አገራት አውሮፕላኖች ጋር ሳይቀላቀል ለጊዜያዊነት በተዘጋጀለት ማረፊያ ቦታ ላይ እንደሚያርፍ ጠቁመዋል።

መንገደኞችም ወደ ዋናው ተርሚናል ሳይመጡ ባሉበት የመጀመሪያ ምርመራ እንደሚደረግላቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። 

በቀጣይም መንገደኞችን አሳፍሮ የመጣው አውሮፕላን በዓለም የጤና ድርጅት ቫይረሱን ለመከላከል በሚረዳ መድሃኒት አውሮፕላኑ ውስጣዊና ውጫዊ ክፍሉ እንዲረጭ ይደረጋል ነው ያሉት።

የእጅ ንኪኪ በሚኖርባቸው የአውሮፕላኑና የተርሚናሉ አካባቢዎች ላይም ኬሚካል እንደሚረጭ የገለጹት ምክትል ፕሬዝዳንቱ የቁጥጥር ስርአቱ በጥንቃቄ የሚመራ ነውም ይላሉ።

በአሁኑ ወቅት በኢትዩጵያ በቫይረሱ ተጠርጥሮ በለይቶ ማቆያ ማዕከል ያለ ሰው አለመኖሩን ከኢንስቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በአሁኑ ወቅት ከ80 ሺህ በላይ ሰዎች በኮቪድ-19 ወይም ኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል ፤ 2 ሺህ 700 ሰዎች በላይ ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም