በውሃ ደህንነት ላይ የተደቀኑ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ተጠቆመ

106

አዲስ አበባ የካቲት 16/2012 ኢዜአ በውሃ ደህንነትና አጠቃቀም ላይ የተደቀኑ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ ተጠቆመ። 

በውሃ አያያዝና ደህንነት ዙሪያ ትኩረት ያደረገው ሁለተኛው ዓለም አቀፍ ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሣ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ውሃን በአግባቡ መጠቀምና ለአገር እድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ማስቻል አስፈላጊ ነው፡፡

የሰዎች አኗኗርና ህይወት ከውሃ ጋር የማይቋረጥ ተፈጥሯዊ ቁርኝት እንዳለው የሚታወቅ ቢሆንም ውሃ ለታዳሽ ኃይል ምንጭነትም በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። 

በመሆኑም የውሃ ሃብትን በአግባቡ ለመጠቀመም የሚደረጉ ጥናቶች አስፈላጊ መሆናቸውን ዶክተር ካባ ገልጸዋል፡፡

ይህ ጉባኤም በውሃ አጠቃቀምና ህልውና ላይ የተደቀኑ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ በአባይ ተፋሰስ፣ አዋሽ ተፋሰስና በስምጥ ሸለቆ ተፋሰሶች ላይ ጥናት እያደረገ  መሆኑም ታውቋል።

በጥናቱ ወንዞች የሚበከሉባቸው ዋነኛ ምክንያቶች ምን እንደሆኑና የብክለት መጠናቸው ምን ያክል እንደሆነ ማወቅ ያስችላል ተብሏል።

በጥናቱ መሰረት ችግሮች ተለይተው የመፍተሄ ሃሳቦች ተግባራዊ የሚደረጉ ሲሆን ለፖሊሲ አውጭዎችም ግብአት እንደሚኖረው ታምኖበታ።

በውሃ አያያዝና ደህንነት ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገው ዓለም አቀፉ ጉባኤ "የውሃ ደህንነት ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ ከዛሬ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ ይሆናል።

የውሃ ደህንነት ለዘላቂ ልማት የፕሮጀክት በኢትዮጵያ፣ ብሪታኒያ፣ ማሌዥያ፣ ህንድ እና ኮሎምቢያ አስተባባሪነት የሚመራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም