መንግስት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮችን እንዲፈታላቸው የመቅደላ ወረዳ ነዋሪዎች ጠየቁ

78

ደሴ፣ የካቲት 16/2012 (ኢዜአ)  መንግስት የጀመረውን የመሰረተ ልማት ግንባታ በማጠናከር በአካባቢያቸው የሚስተዋሉ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮችን እንዲፈታላቸው በአማራ ክልል የደቡብ ወሎ ዞን የመቅደላ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ። 

ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እንዲፈቱ የአካባቢውን ሰላም መጠበቅ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ ደመቀ መኮነን አስገንዝበዋል።

በወረዳው የማሻ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አህመድ ይመር እንደገለጹት መንግስት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ፣ ሆስፒታልና ደብብ ወሎን ከደቡብ ጎንደር የሚየገናኝ መንገድና የበሽሎ ወንዝ ላይ ድልድይ መገንባቱ የዘመናት ጥያቄያቸው ተቀርፏል።

ይሁን እንጅ የመቅደላ ወረዳ ዋና ከተማ የሆነችው የማሻ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የመብራት መቆራረጥና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ያልተሟሉላት በመሆኑ ህብረተሰቡ በውሃ ጥምና ሌሎች ችግሮች ውስጥ ይገኛል።

የማሻ ከተማ ዋና መንገድ አስፓልት እንዲሆንና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች በጌጠኛ ድንጋይ እንዲገነቡላቸው ለወረዳው ጥያቄ ቢያቀርቡም እስካሁን ስላልተፈታ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ከደቡብ ጎንደር ዞን የሚያገናኘውና ከጊንባ በተንታ በኩል የሚሰራው አስፋልት መገንጠያ እስከ ማሻ ከተማ ያለው 27 ኪሎ ሜትር መንገድ ወደ አስፓልት መንገድ ሊያድግልን ይገባል ብለዋል።

ሌላዋ የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ሩት አስፋው የከተማዋ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ኮብል አለመሆን የሥራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነት፣ የመኖሪያ ቤት መገንቢያ ቦታ እጥረትና የህግ የበላይነት አለመከበር ዋና ችግሮች ናቸው ብለዋል።

የተገነቡት ሆስፒታሉና ቴክኒከክ ሙያ ኮሌጅም በበቂ ቁሳቁስ ያልተሟላላቸው በመሆኑ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዳልቻሉ ጠቁመው ችግሮቹን የፌደራልና የክልሉ መንግስት እንዲቀርፍላቸው ጠይቀዋል።

የተመረቁ የልማት ፕሮጀክቶችን ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ጥበቃ ከማድረግ ባሻገር  በቀጣይ መንግስት በሚያካሂደው የልማት እንቅስቃሴ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚስተር አቶ ደመቀ መኮነን በበኩላቸው ህብረተሰቡ ያነሳቸው የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች በየደረጃው እንዲፈቱ የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ በጋራ መቆም ይገባል።

በጀመርነው የብልጽግና ጉዞ የማይፈታው ጥያቄ አይኖርም ያሉት አቶ ደመቀ ጉዟችን በጥቅመኞችና በለውጡ አደናቃፊዎች እንዳይገታ ህዝቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል አለበት።

ይህም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ተደጋግፈን፤ ተረዳድተንና ተመካከረን ኢትየጵያን ወደ ከፍታ የምንወስድበት እንጅ የምንጠላለፍበት፣ የምንተቻችበትና የምንናቆርበት ዘመን መሆን የለበትም ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የመቅደላ ወረዳ ህዝብ ላደረገው ደማቅ አቀባበልና ክብር ምስጋናቸው አቅርበዋል።

በክልሉ የሚካሄዱ የውሃ፣ የስራ እድል ፈጠራና ሌሎች የልማት ስራዎችን ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ የክልሉ መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በህብረተሰቡ ወደ አስፓልት ይደጉልን የተባሉ መንገዶችን ከፌደራል መንግስት ጋር ተነጋግረን ለመስራት ጥረት እናደርጋለን ብለዋል፡፡

በሐሰትና አሉቧልታ መረጃ አገር ለማፍረስ የሚሰሩ ኃይሎችን በጋራ ታግለን መመከት አለብን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ህብረተሰቡ በስሜት ከመጓዝ ይልቅ ምክንያታዊነት አስተሳሰብን ማጎበት አለበት ብለዋል።

የፌደራል፤ የክልልና የዞን አመራሮች በተገኙበት በ87 ሚሊዮን ብር የተሰሩ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን መመረቃቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም