ዓለም አቀፍ የሆርቲካልቸር ጉባዔ በመጪው ዓርብ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

80

የካቲት 16/2012 ኢትዮጵያ በአበባ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ዘርፍ ያለውን ችግር ለመፍታት የሚያግዝ ዓለም አቀፍ የሆርቲካልቸር ጉባዔ ልታዘጋጅ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

አገሪቷ ለሆርቲካልቸር ምርት ምቹ የአካባቢ ሥነ ምህዳር ቢኖራትም ዘርፉን በአግባቡ እየተጠቀመችበት እንዳልሆነም ተነግሯል።

የግብርና ሚኒስቴር የካቲት 21 እና 22 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የሆርቲካልቸር ጉባዔ በማስመልከት ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ እንደገለጹት፤ ሆርቲካልቸር በስራ ዕድል ፈጠራና በአገራዊ ኢኮኖሚ ላይ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ ነው።

ኢትዮጵያም እንደ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ያሉ የሆርቲካልቸር ምርቶችን ማልማት የሚያስችል ምቹ ሥነ ምህዳር እንዳላት ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ በዘርፉ መፍጠር የሚገባትን የሥራ ዕድልና ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ማግኘት አልቻለችም ብለዋል።

በመሆኑም ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ ዓለም አቀፍ የሆርቲካልቸር ጉባዔ የካቲት 21 እና 22 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

በጉባዔው ከ25 በላይ የዓለም አገራት ላኪዎች፣ አምራቶች፣ ኢንቬስተሮች፣ ገዢዎች፣ ተመራማሪዎችና ሌሎችም የዘርፉ ተዋንያን ይሳተፋሉ ብለዋል።

ሆርቲካልቸር በቀላሉ ቢዝነስ መስራት የሚያስችል ዘርፍ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ጉባዔው በችግሮቹ ላይ ተወያይቶ የመፍትሄ ሃሳብ ለማመንጨት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራች ላኪዎች ማኀበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ በሆርቲካልቸር ምርት ሄደት የሚስተዋለውን ቢሮክራሲ መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ምክክር የሚደረግበት ጉባዔ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም እንደ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ያሉ የኢትዮጵያ የሆርቲካልቸር ምርቶችን ከዓለም ገበያ ጋር ለማስተሳሰር በር ይከፍታል ብለዋል።

ይህ ዓለም አቀፍ የሆርቲካልቸር ጉባዔ "መጪው ጊዜ ሆርቲካልቸርና ሆርቲቢዝነስ ነው" በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም