ሆስፒታሉ የሶስት አምቡላንሶች ድጋፍ አገኘ

95
ሆሳዕና የካቲት 15/2012 በሆሳእና ከተማ የሚገኘው የንግስት ኢሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ሆስፒታል ከጤና ሚኒስቴር የሶስት እምቡላንሶች ድጋፍ ማግኘቱን የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ገለፀ ፡፡ የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ እንደገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሆሳዕና ከተማ ተገኝተው ውይይት ባደረጉበት ወቅት ህብረተሰቡ ያነሳውን የግብአት ይሟላልን ጥያቄ መሰረት በማድረግ የተሰጠ ፈጣን ምላሽ መሆኑን አስረድተዋል ። በህብረተሰቡ ጥያቄ መሰረት ለሆስፒታሉ ስድስት አምቡላንሶች በ 3.6 ሚሊየን ብር ግዢ እንዲፈጸም መወሰኑን ተከትሎ ሶስቱ አምቡላንሶች ተገዝተው ሆሳእና መገባታቸውን ተናግረዋል ። የተቀሩት ሶስት አምቡላንሶች ፣ ሲቲ  ስካንና ኤም አር አይ ማሽኖች በቅርቡ ግዢያቸውን እንደሚፈፀም  የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ገልፀዋል ። የጤና ሚኒስቴር  በድጋፍ የሰጣቸው ሶስቱ  አዳዲስ አምቡላንሶች የአካባቢውን የዘመናት የህክምና አገልግሎት ጥራት ችግር ለማሻሻል ያግዛሉ ብለዋል ። በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የንግስት ኢሌኒ መታሰቢያ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ  ዶክተር አያኖ ሻንቆ በበኩላቸው የአምቡላንሶቹ ድጋፍ  የሆስፒታሉን አገልግሎት ይበልጥ ለማሻሻል እንደሚረዳ ገልፀዋል ። የህብረተሰቡን ጥያቄ መሰረት በማድረግ ለተሰጠው ፈጣን ምላሽም ጠቅላይ ሚኒስትሩን አመስግነዋል ። የሆሳዕና ከተማ ነዋሪ  አቶ አይናለም አበበ እንዳሉት ለሆስፒታሉ የአምቡላንስ ጥያቄ ምላሽ መሰጠቱ የጤና አገልግሎቱን ተደራሽነት ለማስፋት የሚኖረው አስተዋጽኦ የጎላ ነው ብለዋል፡፡ በከተማው ሌላ የአምቡላንስ አገልግሎት የሚሰጥ አካል ባለመኖሩ አምቡላንሶች የአካባቢውን ችግር ከመፍታት አንፃር ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአካባቢውን ህብረተሰብ ላነሳው ጥያቄ ፈጣን ምላሽ በመስጠታቸው የተሰማቸው ደስታ የገለፁት ደግሞ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ኤራሜ ተስፋዬ  ናቸው ። አምቡላንሶቹ የእናቶችንና ህጻናትን እንግልትና ሞት ለመከላከል የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነም ወይዘሮዋ ገልጸዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም