ከ4 ሺህ 896 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን አዲስና ጥገና የአስፓልት መንገድ ስራ ተከናወነ---መንገዶች ባለስልጣን

108
የካቲት 15/2012 (ኢዜአ) ባለፉት ስድስት ወራት ከ4 ሺህ 896 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን  አዲስና ነባር ጥገና  የአስፓልት  ኮንክሪት  መንገድ ስራ መከናወኑ ተገለጸ፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ሀገሪቱን በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር በ2012 በጀት  የመጀመሪያ ግማሽ አመት የ4 ሺህ 896 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን የአዲስ አስፓልት መንገድ ግንባታና ነባር ጥገና ሰራዎችን ማከናወኑንና ገልጿል፡፡ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለኢዜአ እንደገለጹት ከተከናወኑ  የመንገድ ግንባታዎች መካከል  461 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር መንገድ በአዲስ የተገነባ ነው፡፡ ቀሪው 216 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባቸው  ነባር መንገዶች ላይ የተደረገ ከባድ  ጥገና  መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ፤ ከ4 ሺህ 218  ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆነው መንገድ ደግሞ መለስተኛ ጥገና የተደረገለት ነው ብለዋል፡፡ ባለስልጣኑ አከናውነዋለሁ ብሎ ከያዘው  የ6 ሺህ 495  ኪሎ ሜትር እቅድ ጋር ሲታይ በ1 ሺህ 595 ኪሎ ሜትር የነሰ ሲሆን  ክንውኑም 75 በመቶ ነው፡፡ ካለፈው የ2011 በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ደሞ የዘንድሮው 10 በመቶ ብልጫ እንዳለው አቶ ሳምሶን ገልጸዋል፡፡ ባለስልጣኑ ለመንገዶቹ ግንባታ 18 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉንም ነው የጠቀሱት፡፡ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች  የነበሩ ችግሮችና ሌሎች ውስብስብ ሁኔታዎች  ማጋጠሙ በግንባታ ስራው ላይ እንቅፋት እንደነበር የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ በቀሪ ወራት ስራዎችን ከዚህ በተሻለ መልኩ ለመፈጸም ጥረት እንደሚያደረግም ተናግረዋል። በመንግዶቹ የግንባታ ስራ ላይ 58 ሺህ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ የተለያዩ ምክንያቶ በማንሳት ስራ ማጓተት ፣ ከሚገባው በላይ ካሳ መጠየቅና በአግባቡ ሃላፊነትን ያለመወጣት ችግሮች በመኖሩ ፕሮጀክቶች በሁሉም ርብርብና ድጋፍ እንጅ በአንድ ወገን ብቻ የሚተገበር አለመሆኑን ተጠቁሟል። በቀጣይም ሃላፍነታቸውን በአግባቡ የማይወጡ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንና ለዚህ ደግሞ መገናኛ  ብዙሃንም  የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው የህዝብ ግንኙነት ዳሬክተሩ ተናግረዋል። በመንግድ ግንባታ ጥራት መጓደል ጋር  ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን  ቅሬታዎች ለመፍታትም ባለስልጣኑ  ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አቶ ሳምሶን ገልፀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም