በአገራዊ ምርጫው የፖለቲካ ፓርቲዎች መገናኛ ብዙሃን ለሃሳብ ልውውጥና ስርዓቱን የጠበቀ ክርክር ብቻ መጠቀም አለባቸው

74
አዲስ አበባ የካቲት 15/2012 ( ኢዜአ) በቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች መገናኛ ብዙሃንን የሃሳብ ልውውጥና ስርዓቱን የጠበቀ ክርክር ለማድረግ እንጂ ለዘለፋ መጠቀም እንደሌለባቸው ተጠቆመ። ኢዜአ በቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫ የሚዲያ ሚና ምን መሆን እንዳለበት የሚመለከታቸውን አካላትን ጋብዞ ውይይት አድርጓል። ተወያዮቹ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አንዷለም፣ የፎርቹን ጋዜጣ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ታምራት ገብረጊዮርጊስ፣ በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ የሕግ ጥናት ማርቀቅ ዳይሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ እና የሕግ ባለሙያው አቶ ኤፍሬም ታምራት ናቸው። የፎርቹን ጋዜጣ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ታምራት ገብረጊዮርጊስ ''የብሄርተኝነት መጨረሻው የመንግስት ሥልጣንን የመቆናጠጥ ጥም እንጂ ለህዝብ ጥቅም የቆሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች አለመሆናቸውን ያሳያል'' ብሏል። የመገናኛ ብዙሃን አሰላለፍም በብሄርተኞች አሰላለፍ ላይ የተመረኮዘ መሆኑን የገለጸው ጋዜጠኛ ታምራት ፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ተጎጂ የሆኑት በጋዜጠኝነት የሙያ ስነምግባር የሚሰሩ መገናኛ ብዙሃን መሆናቸውን ገልጿል። በጋዜጠኝነት የሙያ ስነምግባር የሚሰሩ መገናኛ ብዙሃን ቢበራከቱ ተገዳዳሪና ተወዳዳሪ ሚዲያዎች የሚኖሩ በመሆኑ የፖለቲካ አውዱ የተረጋጋ ይሆን እንደነበር አብራርቷል። ነገር ግን ጽንፍ በያዙ ፖለቲከኞች ግብግብ የፖለቲካ ከባቢው እንዳይረጋና በዚህ አሰላለፍ ውስጥ የገቡ መገናኛ ብዙሃን ግጭት ቀስቃሽ መሆናቸውን አመላክቷል። በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ የሕግ ጥናት ማርቀቅ ዳይሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ ደግሞ ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ የምርጫ አዋጁን ከምርጫ ቦርድ ጋር በጋራ ተባብሮ መስራቱን ተናግረዋል። የምርጫ ህጉ ላይ ያሉ መብቶችንና ግዴታዎችን ለፖለቲካ ፓርቲዎች የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ ስለመሆኑና በምርጫ ጊዜ መከወን ያለባቸውና የሌለባቸው ተግባራትን ለማስገንዘብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም 100 ለሚሆኑ ዐቃቤያን ሕግ በምርጫ ህጉ ዙሪያ ስልጠና መሰጠቱንና ቀጣዩን አገር አቀፍ ምርጫ ተዓማኒነት ፣ፍትሃዊና ሰላማዊ በሆነ መልክ ለማካሄድ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። የህግ ባለሙያው አቶ ኤፍሬም ታምራት በበኩላቸው ''ከምርጫ በፊትና በኋላ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮች ላይ ባለድርሻ አካላት በጋራ መስራት አለባቸው'' ብለዋል። ተፎካካሪ ፓርቲዎች ደጋፊዎቻቸው ከግጭት ነፃ እንዲሆኑ ማሳሰብ እንደሚገባቸውም አንስተዋል። ፓርቲዎች በድህረ ምርጫ ወቅት ለግጭትና ለፀብ ከሚጋብዙ ድርጊቶች መቆጠብ መቻል እንዳለባቸው ያመለከቱት አቶ ኤፍሬም፤ ከምርጫ በኋላም ግጭት እንዳይፈጠር የዜጎችን ውሳኔ በፀጋ መቀበል ተገቢ እንደሆነ አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አንዷለም ''ፓርቲዎች አሁን ልክ ያልሆኑ ነገሮችን እንዴት ልክ ማድረግ እንደሚችሉ የሀሳብ ትግል ማድረግ አለባቸው'' ይላሉ። ፓርቲዎች በቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫ መገናኛ ብዙሀንን የሃሳብ ልውውጥና ስርዓቱን የጠበቀ ክርክር ለማድረግ እንጂ ለዘለፋ መጠቀም እንደሌለባቸውም አንስተዋል። የሀሳብ ትግላቸው የተሻለ ጤና፣ ትምህርት፣ መሰረተ ልማት፣ ዴሞክራሲ፣ ኢኮኖሚ፣ የተሻለ ሰላምና ደህንነት አመጣለው የሚል ፉክክር እንጂ አንድን ወገን ተጠቃሚ አደርጋለሁ ብለው ፉክክር ውስጥ መግባት እንደሌለባቸው ተናግረዋል። በአገሪቱ ያሉ መገናኛ ብዙሃን በአብዛኛዎቹ መታመማቸውን የገለፁት አቶ ወንድወሰን ፤ አንዱ የሌላው ህመም ላይ ጣት መቀሰር ሳይሆን ሁሉም ራሱን ሊፈትሽና ለሙያ ስነምግባር ተገዥ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል። መገናኛ ብዙሃን የሚዲያ ነፃነትን እየተጠቀሙበት ያለበት አግባብ ልክ ባለመሆኑ ቆም ብለው ራሳቸውን ማየትና ማረም እንደሚገባቸውም ጭምር ነው የገለፁት። የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ቅስቀሳ በሚሰጣቸው ነፃ የአየር ሰዓትና የጋዜጦች አምድ ላይ ከዘለፋ ተቆጥበው ውድ የሆነውን የህዝብ ሀብት ለህዝብ ጥቅም ማዋል እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል። ጋዜጠኞችም ሆነ ፖለቲከኞች ከእነሱ የተሻሉ እድሉን ያላገኙ ሰዎች መኖራቸውን ተገንዝበው የሚያነቧቸውን፣ የሚሰሟቸውንና የሚያዩአቸውን የማህበረሰብ ክፍሎችና ሰዎች ታሳቢ አድርገው እነሱን የሚመጥን ነገር ለማቅረብ ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘባቸውን ቢያፈሱ መልካም መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም