በአፍሪካ ድህነት፣ መፈናቀልና ስደትን ለመቀነስና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን አህጉራዊ መፍትሄ ያስፈልጋል

82
አዲስ አበባ የካቲት 15/2012 ( ኢዜአ) ''በአፍሪካ ድህነት፣ መፈናቀልና ስደትን ለመቀነስና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን አህጉራዊ መፍትሄ ያስፈልጋል'' ሲሉ የተለያዩ አገሮች ባህላዊ አስተዳደር መሪዎች ገለጹ። ኢዜአ ያነጋገራቸው የካሜሩን፣ ጋና ኮትዲቯር የባህላዊ አስተዳደር መሪዎች እንደገለጹት፤ በአህጉሩ ለሚታዩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት ባለመቻሉ ግጭት፣ መፈናቀልና ስደት መቀነስ አልተቻለም። የአፍሪካ አገሮች የተሻለ ኢኮኖሚያዊ እድገት እያሳዩ ቢመጡም በተለያየ ጊዜ በሚነሱ የሰላም መደፍረስ ዘላቂ ሰላም እንዳይሰፍንና ልማት እውን እንዳይሆን መሰናክል መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም እነዚህም በአፍሪካ ስጋት የሆኑትን ጉዳዮች ለመፍታት በተለይ የአህጉሩ መሪዎች በትብብር መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። በተለይም አገሮች የውስጣቸውን ሰላም ከጎረቤት ጋር በመቀናጀት መጠበቅ እንዳለባቸው አመልክተዋል። በካሜሮን የባህላዊ አስተዳደር መሪ ዶክተር ሮቢንሰን ታኒዬ እንደሚሉት፤ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት በተለይ ባህላዊ የአመራር ዘዴዎችን መጠቀም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። ለባህላዊ ግጭት አፈታት ዘዴዎች ትኩረት በመስጠት ግጭቶችንና ሌሎች ማህበራዊ ቀውስ የሚያስከትሉ ጉዳዮችን በቅንጅት መፍታት እንደሚገባ አሳስበዋል። የጋና ባህላዊ አስተዳደር መሪ ናና አዩሜዱ በበኩላቸው፤ የተማረ ሰው ድህነትን መቀነስና አገርን መቀየር ይችላል ባይ ናቸው። በዚህም በተለይ የዲያስፖራው ማህበረሰብ የተሻለች አፍሪካን ለመገንባት ትልቅ ሚና ያለው በመሆኑ በአግባቡ ተቀብሎ ማስተናገድ እንደሚገባ አመልክተዋል። በአህጉሩ ያለውን ነባር ባህላዊ አስተዳደር ከዲያስፖራው ተሞክሮ ጋር በማዋሃድ ዘመናዊ አፍሪካን እውን ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል። የኮትዲቭዋር ባህላዊ አስተዳደር መሪ ዶክተር ቺፊዚ ጀንደርቫ፤ አፍሪካውያን ራሳቸው አፍሪካን ለመቀየር ቁርጠኛ መሆን እንዳለባቸው ይገልጻሉ። የአፍሪካ አገሮች የእርስ በርስ ትስስር ፈጥረው ህዝብን በማሳተፍ ለችግሮች መፍትሄ እንዲያመነጩ ለማስቻል የበኩላቸውን ለማበርከት እየሰሩ እንደሚገኙ አመልክተዋል። ለአብነትም በኮትዲቭዋር የኢትዮጵያ አምባሳደር የተሳተፉበት ህዝባዊ የውይይት መድረክ አዘጋጅተው እንደነበር አስታውሰዋል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን 'ለአፍሪካውያን ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ' በሚል መርህ መሰረት ለአህጉሩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍትሄ ለማመንጨት እንደሚሰሩ ይታወቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም