ሕዝበ ክርስቲያኑ ዓቢይ ጾምን ለአገሩ ሰላምና አንድነት በመማለድ እንዲያሳልፍ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ሕዝበ ክርስቲያኑ ዓቢይ ጾምን ለአገሩ ሰላምና አንድነት በመማለድ እንዲያሳልፍ ተጠየቀ
54
አዲስ አበባ የካቲት 15/2012 ( ኢዜአ) ሕዝበ ክርስቲያኑ ዓቢይ ጾምን ለአገሩ ሰላምና አንድነት በመማለድ እንዲያሳልፈው የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አሳሰበች። የኢትዮጵያ ካቶሊካውያን ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል ዓብይ ጾምን ምክንያት በማድረግ ለእምነቱ ተከታዩች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ካርዲናል ብርሃነየሱስ በመልዕክታቸው ''ምዕመናን ወርሃ ጾሙን ለአገር ሰላምና አንድነት ፈጣሪን በመማለድ ማሳለፍ ይጠበቅባቸዋል'' ብለዋል። ''ጾም ለራስ ብቻ ከማሰብ ወጥተን በፈጣሪ ምሕረት ያገኘነውን የመንፈስ እርካታ ለሌሎች የምናስተላልፍበት የመቀራረብ፣ የመተሳሰብ፣ የመዋደድና እርስ በርስ በይቅርታ የምንጠያየቅበት ነው'' ሲሉ አመልክተዋል። በጾም ወቅት ልግስናን በመፈጸም በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን መርዳት እንደሚያሻ ካርዲናሉ ገልጸዋል። ''ወቅቱ በተለይ የእግዚአብሔር ፍቅርና እንክብካቤ የሚያሻቸውን ድሆችን፣ በሕመም ምክንያት የሚሰቃዩትንና አረጋውያንን የምንጎበኝበት ሊሆን ይገባል'' ብለዋል። ወላጆችም በዚሁ ወቅት ለልጆቻቸው መልካም ስነ-ምግባርን በማስተማር፣ በቤት ውስጥ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ማበረታታት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። በተጨማሪም ልጆች በዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂ በመጠመድ የሚያባክኑትን ጊዜ በአግባቡ ስራ ላይ እንዲያውሉት በመቆጣጠር ሌሎችን እንዲንከባከቡና ያላቸውን ማካፈል እንዲለማመዱ ወላጆች እንዲሰሩ መክረዋል። በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስና የካቶሊክ ክርስትና እምነት ተከታዮች ለ55 ቀናት የሚቆየውን ዓቢይ ፆም ነገ ይጀምራሉ።