የመደመር አስተሳሰብና የብልጽግና ጉዞውን እንደሚደግፉ የምእራብ ሸዋ ነዋሪዎች ገለፁ

66
አምቦ የካቲት 15/2012 (ኢዜአ) የምእራብ ሸዋ ዞን ነዋሪዎች የመደመር አስተሳሰብና የብልጽግና ጉዞውን ለማስቀጠል የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ዛሬ ባካሄዱት ሰልፍ ገለጹ። ነዋሪዎቹ በአምቦ ከተማ ዛሬ ባካሄዱት የድጋፍ ሰልፍ ለውጡን የሚያበረታቱ የተለያዩ መፈክሮችን አሰምተዋል ። በሰልፉ ላይ በሀገር ውስጥና በጎረቤት ሀገራት ጭምር ለውጥ እያመጣ ካለ መሪ ጎን እንቆማለን! መጪው ጊዜያችን ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ብሩህ ነው! ከብልፅግና ጎን ቆመን ሀገሪቷን እናሻግራታለን! የሚሉና ሌሎች የድጋፍ መፈክፎች በብዛት ተስተጋብተዋል ። ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ የሰላም አባትና አምባሳደር በመሆናቸው ራዕያቸውን ለማሳካት ድጋፋችንን እናጠናክራለን ሲሉ የሰልፉ ተሳታፊዎች ተናግረዋል ። በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለው የፀጥታ ችግር እልባት እንዲያገኝም ሰልፈኞቹ  ጠይቀዋል፡፡ የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲሪብሳ ዋቁማ ለሰልፈኞቹ ባሰሙት ንግግር ለውጡን ለማስቀጠል ከዶክተር አብይ አመራር ጋር መቆም አስፈላጊ በመሆኑ ሰልፈኞቹ ያሳዩት ፍላጎት የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል ። የዞኑ ነዋሪ አንድነቱን አጠናክሮ ለብልፅግና ጉዞው መሳካት ድጋፉን እንዲቀጥልም አሳስበዋል፡፡ ህብረተሰቡ የጀመረውን ድጋፍ በማጠናከር ለሀገር ግንባታው የሚጠበቅበትን እንዲወጣም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ህብረተሰቡ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ የሚሞክሩ አካላትን በማጋለጥ ከብልጽግና ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡ በሰልፉ ላይ ከዞኑ ወረዳዎች የተውጣጡ አባቶች፣ እናቶች፣ ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ አባገዳዎችና የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም