በመቅደላ ወረዳ የተገነቡ መሰረተ ልማቶች ተመረቁ

89
ደሴ፤ የካቲት 15/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን መቅደላ ወረዳ የተገነቡ መሰረተ ልማቶች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህና ከፍተኛ ሃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ተመረቁ ። የመቅደላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ሞላ ለኢዜአ እንዳስታወቁት የመሰረተ ልማቶቹ ከ2007 ዓ.ም  ጀምሮ በ87 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ ናቸው። በምረቃው ስነ ስርዓት ላይ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል ። ዛሬ ከተመረቁት መሰረተ ልማቶች መካከል የመቅደላ ማሻ የመጀመሪያ ደረጀ ሆስፒታልና የመቅደላ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ይገኙበታል ። የደቡብ ወሎንና ደቡብ ጎንደር ዞኖችን የሚያገናኘው "በበሽሎ" ወንዝ ላይ የተሰራው 150 ሜትር ርዝመት ያለው ድልድይም ዛሬ ከተመረቁት መሰረተ ልማቶች መካከል አንዱ ነው ። የድልድዩ ግንባታ ሁለቱን ዞኖች ከማገናኘቱም ባለፈ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩን የሚያጠናክር ነው ብለዋል። በምረቃ ስነ ስርዓቱም ከክልሉና የፌደራል ከፍተኛ አመራሮች በተጨማሪ የአካባቢው ነዋሪዎችና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል። ከሰዓት በኋላም አመራሮቹ በማሻ ስታዲዮም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በልማት፣ በመልካም አስተዳደርና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር እንደሚያደርጉ ከወጣው ፕሮግራም ለመረዳት ተችሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም