ለውጡ የመስዋእትነታችን ውጤት በመሆኑ ለውጤታማነቱ ዘብ እንቆማለን -- የአዳማና አካባቢው ነዋሪዎች

62
አዳማ የካቲት 15/2012 (ኢዜአ) ከአዳማ ከተማና ከ10ሩ የምስራቅ ሸዋ ዞን የገጠር ወረዳዎች የተወጣጡ ነዋሪዎች ለውጡን ለማስቀጠል የበኩላቸው ድጋፍ እንደሚያደርጉ ለመግለፅ   ሰልፍ አካሔዱ። ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡት የሰልፉ ታዳሚዎች መካከል አቶ ረሂም አለሙ እንደገለጹት ለውጡ እኛም መስዋትነት የተከፈለበት ነው ብለዋል። ዶክተር አብይ በሀገራችን ካየናቸው መሪዎች በተለየ መልኩ ፍትሃዊ መሪ ናቸው ያሉት አቶ ረሂም ከሁለት ዓመት በፊት ህዝባችንና ሀገራችን  ምን ያክል አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው እንደነበር ከገፈት ቀማሾቹ አንዱ ስለነበርኩኝ ህያው ምስክር ነኝ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ። አሁን ያለውን ነፃነትና የሰላም አየር ለማስቀጠል ከለውጡ ጎን መሆናቸውን ለመግለፅ ሰልፉ ላይ መገኘታቸውን ጠቅሰው እንድሰውብቻውን ለውጡን ማስቀጠልና ሰላምን ማስጠበቅ ስለማይችል ከጠቅላይ ሚኒስትራችን ጎን መቆማችንን ለማረጋገጥ ሰልፍ ወጥተናል ብለዋል። ዶክተር አብይ በሀገሪቷ ውስጥ በአጭር ጊዜ ያመጡትን ለውጥ ለመደገፍ ነው እዚህ የተገኘሁት ያሉት ደግሞ አቶ ወንድሙ አብቹ የተባሉ ነዋሪ ናቸው። ዶክተር አበይ አህመድ ከዚህ በፊት ከነበሩት መሪዎች በተለየ ተጨባጭ ለውጥና ውጤት ያስመዘገቡ መሪ በመሆናቸው አገሪቱ ወደብልፅግና ጎዳና እንደሚወስዱዋት በመተማመን ድጋፋችንን ለመግለፅ በፍላጎታችን ሰልፍ ወጥተናል ብለዋል። ከመደመርና ብልፅግና ውጪ ሌላ አማራጭ የለም ያሉት አቶ ወንድሙ በሀገራችን ያለው ለውጥ ተጨባጭና በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ያለንን ተቀባይነት ከፍ ያደረገ መሆኑን ገልፀዋል ። የተጀመረው ለውጥ ከግብ እንዲደርስ ህዝቡ ከጠቅላይ ሚኒስትራችን ጎን በመቆም መደገፍ፣ማገዝና የድርሻውን ማበርከት እንደሚገባውም አቶ ወንድሙ ተናግረዋል። ሀገራችን የሚያስፈልጋት በአስተሳሰብ የተሻና የበለጠ ለውጥ የሚያመጣ መሪ በመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የመደመር እሳቤ ለመደገፍ ሰልፍ ወጥተናል ያሉት ደግሞ አቶ መኮንን ዑርጋ ናቸው። የተሻለ አስተሳሰብና አካሄድን መደገፍ ለሀገራችን እድገትና ብልፅግና አስፈላጊ ነው ያሉት አቶ መኮንን ጠቅላይ ሚኒስትራችን የያዙት ሃሳብና ራዕይ አሸናፊ በመሆኑ ከጎናቸው እንቆማለን ብለዋል ። የአዳማ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ሙሐመድ ጉዮ በበኩላቸው ብልፅግና መሰረቱ እውነተኛ ሕብረ ብሔራዊ እንድነት በመሆኑ ከብሔር ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመሆን ለውጡን ለማስቀጠል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በሙሉ አቅማችን እንሰራለን ብለዋል። የለውጡ ባለቤትና መሪ ህዝቡ መሆኑን የአዳማ ከተማና Yምስራቅ ሸዋ ዞን ነዋሪዎች በሰልፉ ማስመስከራቸውንም አቶ መሀመድ ተናግረዋል። ለውጡ ፍሬያማ እንዲሆንና ከትሩፋቱ ለመቋደስ በትግላችሁ ያገኛችሁትን ለውጥ መጠበቅና መንከባከብ ብሎም ሽግግሩን ስኬታማ ለማድረግ ሁላችሁም ከብልፅግና ፓርቲ ጎን በፅናት እንድትሰለፉ ጥሪየን አቀርባለሁ ሲሉም ከንቲባው መልእክት አስተላልፈዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም