መርሃ ግብሩ ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ የማሸጋገር ጽኑ ፍላጎት ማሳያ ነው - ሰላም ሚኒስቴር

74
አዲስ አበባ የካቲት 15/2012 ( ኢዜአ) “በጎነት ለአብሮነት” በሚል መሪ ሀሳብ የመጀመሪያው ብሔራዊ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት መርሃ ግብር ማብሰሪያ ስነ-ስርዓት ዛሬ በአፍሪካ ህብረት ተካሂዷል። በስነ-ስርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት ተወካዮች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድር፣ ሚኒስትሮች፣ የህብረተሰብ ተወካዮችና ወጣቶች ተገኝተዋል። በስነ-ስርዓቱ ላይ የሰላም ሚኒስትሯ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በየምዕራፉ ባለፈችባቸው የታሪክ ሂደቶች የየዘመኑ ወጣት ሴቶችና ወንዶች ሚናና አሻራ ድርሻ ነበረው። ''የየዘመኑ ወጣቶች ስልጣኔን ሲያንጹ፣ አገርን ከጠላት ሲከላከሉ፣ ለማህበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች መሻሻል ለውጥን ሲመሩና ሲታገሉ ኖረዋል'' ብለዋል። መርሃ ግብሩ የወጣቶች አገር የማገልገልና ኢትዮጵያን ወደ አንድ አዲስ ምዕራፍ የማሸጋገር ጽኑ ፍላጎት ማሳያ እንደሆነ የገለጹት ወይዘሮ ሙፈሪያት፤ የኢትዮጵያ የዕድገት መሰረት የሆነው ወጣት ሃይል ታላቅ ትሩፋት መሆኑን አመልክተዋል። ወጣትነት ውስጥ ያለውን እምቅ ሃይል ለማስተዳደር፣ ለመምራትና ለመግራት ብሎም ወጣቱ ራሱን ፍለጋ እንዲተጋ ለማድረግ ወጣትነትን ማበልጸግ እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል። ይህም የወጣቱን የአገር ፍቅርና ሰላም ወዳድነት በማረጋገጥ ለአገሩ ትውልዳዊ አሻራ እንዲያኖር ዕድል ይፈጥራል ብለዋል። ''የአገራችን ወጣቶች የነገ ብቻ ሳትሆኑ የዛሬም የነገም ናችሁ'' ያሉት ሚኒስትሯ፤ ራስን፣ አካባቢንና አገርን ማወቅና መረዳት ከዘላቂ ሰላምና አገር ግንባታ አንጻር የጎላ ፋይዳ እንዳለው አስገንዝበዋል። የወጣቱ ፋይዳ የጎላ በመሆኑም ሚኒስቴሩ በመርሃ ግብሩ ወጣቱን ለማሳተፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ዝግጅት ማድረጉን ወይዘሮ ሙፈሪያት ገልጸዋል። ለአገልግሎቱ አምስት የበጎ ፈቃድ አምባሳደሮች ተመርጠዋል፤ ከመላ አገሪቷ የተውጣጡ ከ116 ሺህ በላይ ወጣቶችም ተመዝግበዋል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የሚሰጠው መንግስታዊ ካልሆኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በመተባበር እንደሆነም ተገልጿል። መርሃ ግብሩ የዜጎችን አብሮ የመኖር እሴት ያዳብራል። 10 ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በመጀመሪያው ዙር ለሁለት ወራት እንደሚሰለጥኑ ታውቋል። በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የሚሳተፉ ወጣቶች ከሚያገኙት እርካታ በተጨማሪ በተለያዩ ተቋማት መቀጠር የሚያስችላቸው የስራ ልምድ ይሰጣቸዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም